| “በቅንጅት ሰም ጠቅላላ ጉባኤ እንጠራለን፤ ምርጫ ቦርድም እን |
|
|
| Thursday, 17 January 2008 | |
|
“በቅንጅት ሰም ጠቅላላ ጉባኤ እንጠራለን፤ ምርጫ ቦርድም እንከሳለን” አቶ አባይነህ ብርሃኑ- ከጌታቸው ንጋቱ የቅንጀት ለአንድነትና ለዴሞክራሲን ፓርቲ ሕጋዊ ሠርተፌኬት ለአቶ አየለ ጫሚሶ መሠጠቱን ተከትሎ ምርጫ ቦርድን ውሣኔ በመቃወም ወደ ፍርድ ቤት ለመሄድ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን አቶ አባይነህ ብርሃኑ አስታወቁ፡፡ በቅርቡም በቅንጅት ስም ጠቅላላ ጉባዔ እንደሚጠራ ገለፁ፡፡
“የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጠቅላላ ጉባዔ ጠርታችሁ አመራር መርጣችሁ ስትመጡ ሕጋዊ ሠርተፊኬቱን እንሠጣችኋለን ሲል ከርሞ በደባ ቅንጅትን ለማይወክሉ ሰዎች እውቅና ሠጥቻለሁ ማለቱን ፈፅሞ አንቀበለውም፡፡ የሕግ ኮሚቴችን ጉዳዩን በሕግ ለመጠየቅ ዝግጅት እያደረገ ነው” በማለት የተናገሩት አቶ አባይነህ “የቅንጅትን ስምና ምልክት ከፋፍሎ በመስጠት በሕዝብ ልብ ውስጥ ያለውን ፓርቲ ለማጥፋትና ለማከሠም ሆነ ተብሎ የተሰራ ሴራ ነው፡፡ የቅንጅት ሠርተፊኬት ምርጫ ቦርድ የሠጣቸው ሰዎች ቅንጅትን የማይወክሉና መንፈሳቸውም የቅንጅት ያልሆነ፤ በሌላ አካል ተልዕኮ የተሠጣቸው ናቸው” በማለት ገልፀዋል፡፡ በቅርቡም በቅንጅት ስም ጠቅላላ ጉባዔ እንደሚጠራ ያስታወቁት አቶ አባይነህ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ከ40 በላይ የቅንጅት ተመራጮች በየወረዳው እየተንቀሣቀሡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወደፊት በሚጠራው ጠቅላላ ጉባዔው ፕሬዚዳንታቸው ኢ/ር ኃይሉ ሻውል እንደሚገኙ ያስታወቁት አቶ አባይነህ ኢ/ር ኃይሉ በመልካም ጤንነት ላይ እንዳሉ ባለፈው እሁድም ለሁለተኛ ጊዜ በአትላንታ የቅንጅቱን ደጋፊዎች ማነጋገራቸውን አስታውቀዋል፡፡ የቅንጅት ሕጋዊነት ለአቶ አየለ መሠጠቱን” ሲጠበቅ የነበረና አዲስ ያልሆነ ውሣኔ መሆኑን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ባለፈው ሣምንት በአቶ አየለ ጫሚሶ ለሚመራው ቡድን የቅንጅትን ሕጋዊ ሠርተፊኬት መስጠቱን መግለፁ ይታወሳል፡፡ ከውሣኔው ጀርባ የሌሎች ፍላጐት አለበት፡፡ በስሙ የተመረጥን፣ ሰዎች እያለን ለሌላ ተግባር የተሠናዱ ሰዎች መርጦ እውቅና ሠጠሁ ማለት ተቀባይነት የለውም” ሲሉም አቶ አባይነህ አስረድተዋል፡፡
ከአቶ አየለ ጫሚሶ ጋር ተደራድረው አብረው ለመስራት እንደሚያስቡም ተጠይቀው “ይኼ መቼም ሊሆን አይችልም፡፡ እነሱ የቅንጅት ሰዎች አይደሉም፡፡ የቅንጅትም መንፈስ የላቸውም፡፡ ከነሱም ጋርም ድርድር የምናደርግበት ምንም ዓይነት መሠረታዊ ጉዳይ የለም፡፡ የነሱ አጀንዳ ቅንጅት ማጠናከር ሣይሆን ከጀርባ የተላኩበትን ዓላማ ማሣካትና ቅንጅትን ማዳከምነው” ሲሉ መልሠዋል፡፡ በቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ሥም ተመርጠው ፓርላማ የገቡ ተመራጮች አዲስ ፓርቲ እስኪቋቋም ድረስ በፓርላማው የሥነ ምግባርና አሰራር ደንብ አንቀፅ 181 መሠረት በቡድን ለመንቀሳቀስ መወሰናቸውን የገለፁት አቶ ተመስገን ዘውዴ ከወ/ሪት ብርቱካን ቡድን ጋር እያደረጉ ያለው ድርድር በተሳካ ሁኔታ መቀጠሉንና አዲስ ፓርቲ በማቋቋም የተነሱለትን ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግል ከዳር ለማድረስ ቆርጠው መነሳታቸውን አስታውቀዋል፡፡ የምርጫ ቦርድን ውሳኔ ፍትሃዊ አለመሆን የገለፁት አቶ ተመስገን ከአቶ አየለ ጫሚሶ ጋር የሚደራደሩበት ምንም ምክንያት አለመኖሩንና ሕዝቡም ትክክለኛው የቅንጅት አራማጅ ማን እንደሆነ ስለማያውቅ አዲስ ፓርቲ አቋቁሞ ትግሉን መቀጠል አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሚመሰረተው ፓርቲ ስያሜ፣ ሰራዎቹ የሚፈፀሙበት የጊዜ ሰሌዳ ገና እየተወያዩበት መሆኑን፣ ሁሉም ነገር መልክ ሲይዝ ለሕዝብ እንደሚያሳውቁ አቶ ተመስገን ተናግረዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አየለ ጫሚሶ የሥም ማጥፋት ዘመቻ እየተደረገባቸው መሆኑን ሲገልፁ “የኢሕአዴግ ተለጣፊዎች ናቸው እያሉ የኛን መልክ ጥላሸት ከመቀባት ወደ ፓርቲያቸው መጥተው ቢሰሩ ይሻላል፡፡ ሁሉም መምጣትና መስራት ይችላሉ፡፡ ስም ማጥፋት የትም አያደርሰንም፡፡ ስልጣን ከሆነ የሚፈልጉት ወደ ፓርቲው መጥተው የፈለጉትን ያገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቡ ላይ መቀለድ ይብቃ” ብለዋል፡፡
ለኢዴአፓ-መድሕን በተሰጠው የቅንጅት የጣት ምልክት ምትክም በሚቀጥለው ምርጫ የሚሳተፉበትን አዲስ ምልክት ለምርጫ ቦርድ ማሳወቃቸውን የገለፁት አቶ አየለ ሁለት ሰዎች ተጨባብጠው ያሉበት ምስል ለምርጫ መወዳደሪያነት ማቅረባቸውንና ዕጩዎቻቸውንም በቅርቡ እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል፡፡ Comments (0)
![]() Write comment
|