በኢትዮጰያ ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ/ም በተካሔደው በተወካዮችና
ክልል ምክር ቤት ምርጫ በሀገር አቀፍ ደረጃ ማሸነፋ በስፋት የተነገረለት የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፖርቲ የደቡብ
ኢትዮጰያ አደራጅ ቡድን በአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ ጥር 6 ቀን 2ዐዐዐ ዓ/ም ከቀኑ 11 እስከ ምሽቱ 2፡3ዐ ድረስ ታስሮ
ተለቀቀ፡፡
በቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፖርቲ የጠቅላላ ጉባዔ አባል በሆኑት
በአቶ ታዴዎስ ታንቱ የተመራው ይህ አደራጅ ቡድን ተይዞ ሊታሰር የበቃው በጋሞ ዞን በአርባ ምንጭ ከተማ የፖርቲውን ሕጋዊ
ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውጤታማ ለማድረግ ከዞኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በአንድ የመሰብሰቢያ ሥፍራ ውይይት
በሚያካሔድበት ወቅት በተደረገበት ከበባ ነው፡፡
በዕለቱ የመቶ አለቃ አንተነህ አበበ የአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ አዛዥ
ቡድኑን ሕጋዊ የፈቃድ ደብዳቤ የጠየቁ ሲሆን፣ አቶ አቤል ሙሴ የተወካዮች ምክር ቤት አባል የያዙትን ደብዳቤ ወዲያው አውጥተው
ያሳዩ ቢሆንም በአዛዡ በኩል ደብዳቤው ተቀባይነት አጥቶ አደራጁ የልዑካን ቡድን እንዲሁም አቶ ገዛኽኝ ገለቱ የዞኑ የሥራ
አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሳቢን ጨምሮ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በሙሉ እስከተለቀቁበት ጊዜ ድረስ ታስረው እንዲቆዩ ተደርገዋል፡፡
በዚሁ ዕለት አቶ ታዴዎስ ታንቱ በእሳቸው የተመራው አደራጅ ቡድን
ኃላፊነቱን የሚወስድ መሆኑን በመግለፅ የዞኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ወዲያውኑ እንዲለቀቁ ለፖሊስ አዛዡ በቃል ያመለከቱ
ሲሆን፣ ታሳሪዎቹ ራሣቸው ግን አደራጁ ቡድን ካልተፈታ ብቻቸውን ለመውጣት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡
በመጨረሻም አዛዡ ሰነዶቻቸውን በማስቀረት እሥረኞቹን በሙሉ ፈትተው
ለቅቀዋቸዋል፡፡
በነጋታው ደግሞ የፖሊስ አዛዡ አደራጁ ቡድን ከሚመለከታቸው አካላት ለፖሊስ
ፅ/ቤት የፈቃድ ደብዳቤ እንዲያመጣለት በማስጠንቀቅ ቀደም ሲል
ከቡድኑ እጅ የወሰዷቸውን ሠነዶች ሁሉ መልሰው ሰጥተውታል፡፡
አንዳንድ ኢትዮጰያውያን የፖለቲካ ተንታኞች የደቡብ ኢትዮጵያ ተዘዋዋሪ
አደራጅ ቡድን "ሕገ ወጥ ስብሰባ አካሔዳችኋል" በመባል ሰለመታሰሩ ከኢትዮጰያ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አያይዘው ሲገልፁ "ገዢው
ሕዳጣን ጎሣ በ1997 ዓ/ም በተደረገው የፖርላማና የክልል እንደራሴዎች ምርጫ ከተሸነፈ ወዲህ የዜጎችን ሰላማዊ እንቅስቃሴ
በየትኛውም ቦታ በማወክ ላይ ይገኛል" ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በደቡብ ኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ወረዳዎች ደኖች
በከፍተኛ ደረጃ በሰደድ እሳት በመውደም ላይ ይገኛሉ፡፡
በዚህም መሠረት በጎፋ ልዩ ዞን ለቀናት በቀጠለው የእሳት ቃጠሎ የማዜ
የእንስሳት መኖሪያ ፖርክ ሙሉ ለሙሉ በመውደሙ በብዙ ሀገሮች ሊገኙ የማይችሉ በርካታ ብርቅና ድንቅ እንስሳት መጠለያ አጥተው
አካባቢውን ለቅቀው ሲሰደዱ የተቀሩት ደግሞ ከተቃጠለው ፖርክ ውስጥ ከቆሙበት ተላላፊ መኪኖችን እንዲሁም እግረኞችን አይተው
በመደንገጥ ጥር 4 እና 5 ቀን 2ዐዐዐ ዓ/ም ሲፈረጥጡ ታይተዋል፡፡
እንዲሁም በዚሁ በጎፋ ልዩ ዞን በቡልቂ ኮረብታ ላይ በተለቀቀው እሳት
በኮረብታው የሚገኝው ደን ጥር 4 ቀን 2ዐዐዐ ዓ/ም ሲቃጠል ውሎ ሌሊትም በተመሣሣይ ሁኔታ ያደረ ሲሆን በነጋታውም ቃጠሎው
እንደቀጠለ ቆይቷል፡፡
በሌላም በኩል በዚሁ በጎፋ ልዩ ዞን በገዜ ኮረብታ ላይ የነበረው ደን
እሳት ተለቅቆበት ጥር 4 ቀን 2ዐዐዐ ዓ/ም ሲቃጠል ውሎ አድሯል፡፡
በተዛመደ መልኩ በዳውሮ ዞን ውስጥ በልዩ ልዩ ኮረብታዎች ላይ ደኖች
እሳት ተለቅቆባቸው ከፍተኛ ቃጠሎ ደርሶባቸዋል፡፡
በደኖች ላይ ይህ ሁሉ ውድመት ሲደርስ " ለሁለት ሺህ ሁለት ዛፍ
በነፍስ ወከፍ" በማለት ሌት ተቀን የሚያላዝነው የወያኔ አምባገነን አገዛዝ ግን ውድመቱን ለመግታት ምንም እርምጃ እንዳልወሰደ
ከአካባቢው ነዋሪዎች ጠይቀን ልንረዳ ችለናል፡፡
|