|
የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፖርቲን ዓላማ ወደ ጎን በመተው
የወያኔ የውስጥ አርበኛ በመሆን፣ በተግባር የሚንቀሳቀሱ ጥቂት የፖርቲው አፈንጋጭ አመራር አባላት ባለፋት ወራት ሕዝቡን
ለማሳሳት በተከታታይ ሙከራዎች ተይተዋል፡፡ ይህ ሙከራቸው ግን በሕዝብ ዘንድ በይበልጥ እንዲጠሉ አድርጓቸዋል፡፡ በተለይ የአዲስ
አበባ ሕዝብ አንቅሮ እንደ ተፋቸው ግልፅ ሆኗል፡፡ በመሆኑም ዛሬ በሕዝብ አገልግሎት መስጫ ሆቴሉችና በሌሎችም መዝናኛ ሥፍራዎች
እንኳን አንዳችም ሰብሰባ እንዳያካሔዱ ተደርገዋል፡፡
ሆኖም ከውድቀታቸው የመማር ብቃት የጎደላቸው አንጀኞቹ አመራሮች አሁንም
ከአሉታዊ ተግባራቸው ለመታቀብ ዝግጁ አይደሉም፡፡ እንዲያውም በአዲስ አበባ ያጡትን ሕዝባዊ ከበሬታ በክፍላተ ሀገር ውስጥ
ለማግኘት አንጃ ግራንጃ የሰነቁ የአሉባልታ ወረቀቶችን እያዥጎረጎሩ በየቦታው ሲበትኑ ታይተዋል፡፡ በዚህ ሒደት በተለይ ስመጥር
የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፖርቲ የአመራር አባላትን ክብር ተዳፍረዋል፡፡ ወደ ራሳቸው ስብዕና እርከን ለማውረድም በብርቱ
ጥረዋል፡፡ ክብርና ሞገስ ያገኙትን አሳንሰው ለማስቀመጥ ባያሌው ተፍጨርጭረዋል፡፡ ለማስረጃም የኢትዮጰያ ሕዝብ ድምፅ ! በሚል
ርዕስ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፖርቲ ኘሬዝዳንትን በማስመልከት ከበተኑት ባለ 6 ገፅ ሐተታቸው በቅድሚያ ይህን
መዝዘናል፡፡ እነሆ !
በምርጫው ሰሞን፣ ለተቃዋሚዎች የሚዲያ ዕድል ሲሰጥ፣
እርስዎ አንድ ቀን እንኳን ቴሌቪዥን ቀርበው ኢህአዴግን
ሳያወግዙ ወይም የኢህአዴግ ባለሥልጣናትን ሳይሞግቱ፣
በሌሎች ትከሻ ላይ ተፈናጠው ታዋቂና ዝነኛ ለመሆን በቁ፡፡
ወቅቱ የግርግር በመሆኑ በኘሮፌሰር አሥራትና በሌሎች
ሰዎች ላይ የፈጸሙት በደል ተድበስብሶ መጥፎ ተግባርዎ
በቅንጅት ታድሶ በሊቀመንበርነት ሹመት የትላንቱን ረስተን
ለአንድ ዓላማ አብረን ተሰለፍን፡፡
ይህ እንግዲህ የአፈነጋጮች የዕውቀት ውኃ ልክ ነው፡፡ ከተሻለ የአስተሳሰብ እርከን ሊመጡ
አይችሉምና፡፡ ምክንያቱም የአዕምሮ አድማሳቸው ይከለክላቸዋል፡፡ ሰለዚህ በልካቸው ለራሳቸው ልክ መሆናቸው ይሰማቸዋል፡፡
ያለማወቃቸውን ሳያውቁ በደረቅ ወኔ የጥፋት ጎዳናን እንደ ትክክል አፅድቀውታል፡፡የፖርቲውን የተግባር መርሐ-ግብርና ሕዝባዊ
ራዕይን ረስተው በግለሰቦች ላይ ዘመቻ ከፍተዋል፡፡ በፍጥነት ወርደዋል፡፡ ማሣቂያና መሣለቂያ ለመሆን በምርጫቸው ቸኩለዋል፡፡
እንደ ሸምበቆ ተመዝዘው ወጥተው እንደ ሙቀጫ ተንከባልለዋል፡፡ በአካሔዳቸው ዓላማቸውን አውጀዋል፡፡ ከስንዴ ማሣ የእንክርዳድ
ነዶ ሆነው ተገኝተዋል፡፡
ዕውን ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል ዝናና ታዋቂነትን የተጎናፀፋት በሌሉች
ትከሻ ተፈናጥጠው ነበር ? እንዴት በዚህ መልኩ ይታሰባል ? ይህ በሁለት እግሩ ቆሞ የሚሔድ ቅጥፈት ነው፡፡ አንጀኞቹ በተግባሩ
ከበሬታ ያገኝን ሰው በአሉባልታ ዝቅ ማድረግ እንደማይቻል ፈፅሞ አልተገነዘቡም፡፡ እንዴ! ምን ማለታቸው ነው? ወያኔን ዕልፍ
አዕላፋት ያወግዙታል፡፡ ወያኔ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በመላው የዓለም ዴሞክራሲያዊ ኃይሎችና ሠላም ወዳዶች ሁሉ
ተወግዟል፡፡ ባሁኑ ወቅት ወያኔን ያላወገዘ ቢኖር ወያኔ ራሱ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ልብ ያለን በልባችን ከልብ ልናስተውል
ይገባል፡፡ ወያኔን ያወገዘ ሁሉ ታዋቂነትን አይጎናፀፍም፡፡ ምላስ ተግባር አይደለምና፡፡ ይህን የትውልድና የታሪክ ጠላት
የሆነውን ሰው በላ አውሬ ለማስወገድ በቁርጠኝነትና በዓላማ ፅናት ለተግባር መነሣሣት ብቻ ወሣኝ ይሆናል፡፡ እርግጥ ነው!
ዶክተር ብርሃኑ ነጋና ልደቱ አያሌው በምላሳቸው የምላሳቸውን ያህል ተመዝዘዋል፡፡ ዛሬ እነሱን ሰው ሁሉ ያውቃቸዋል፡፡ ድምጻቸው
ትልቅ ምላሳቸው መንታ ነው፡፡ እንደ ባዶ እንሥራ ይጨኻሉ፡፡ የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል ቁም ነገር ግን አይገኝባቸውም፡፡
እናስተውል! ታዋቂነት በራሱ ቁም ነገር ሊሆን ይችላል እንዴ? ፈፅሞ አይሆንም !ያም ሆነ ይህ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ
ፖርቲ ኘሬዝዳንትና ሌሎች ዕውነተኛ የቅንጅት አመራር አባላት በሕዝባዊ ተግባራቸው ታዋቂነትንና ዝናን ተጎናፅፈዋል፡፡ ይልቁንስ
ብዙዎቹ በኘሬዝዳንቱና በትግል አጋሮቻቸው ጠገግ ለታዋቂነት በቅተዋል፡፡ ዕውነታው ይህ ነው! ሰው በተግባር ይለካል፡፡ የዶክተር
በርሃኑ ነጋ ደቀ መዛሙርት ግን የሰውን ትልቅነት ከንግግር አሳማሪነት እርከን ብቻ ያስቀራሉ፡፡ እንዲያውም እንደ ቆርቆሮ የጮኽ
ሁሉ ለእነሱ ትልቅ ሰው ይሆናል፡፡ ለህብረተሰቡ የሚታየው በጎ ነገር ሁሉ ለእነሱ አይታያቸውም ፡፡ በዚህ ምክንያት በጨለማ
ጥቁር መነፅር አድርጎ ከሚጓዝ ሰው ጋር ይመሳሰላሉ፡፡ የአሉባልታ ችሎታቸው ግን ከጣራ ላይ ቆሞ ጣራን ከመመልከት በላይ
አሻቅቧል፡፡ ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል ከወጣትነት ዘመን ዕድሜቸው አንስቶ ለእናት ሀገራቸው በከፍተኛ የሥራ ምድብ በልዩ ልዩ
የኃላፊነት እርከን አስተዋፅኦ ያደረጉ ሰው መሆናቸውን ማንም ሊያስተባብል አይችልም፡፡ ግልፅ ነው፡፡ የኢትዮጰያ ሕዝብ ለብዙ
ዓመታት አሳምሮ ያውቃቸዋል፡፡ ይህ ዕውነታ ተክዶ "...በሌሎች ትከሻ..." ተባለ፡፡ ስም በማጥፋት ስመ-ጥር መሆን ከቶም
እንደማይቻል ግን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
አንጀኞች ቀላሉን ዕውነታ እንኳን ለመረዳት ብቃት ሲጎድላቸው ይስተዋላል፡፡
በዚህ መነሻ ከተጠየቅ ጋር ይጋጫሉ፡፡ ከሕገ ኃሌዮት መርህ ይወጣሉ፡፡ ሐቅ ባለበት የሉም፡፡ ሐሰት በነገሠበት በቀዳሚ ረድፍ
ይታያሉ፡፡ እስቲ እናስብ! እንዴት "...ሚዲያ ዕድል..." ይባላል? እንዴ ! በመገናኛ ብዙሀን ሐሳብን መግለፅ የዜጎች ሁሉ
መብት መሆኑ እንዴት ይታጣል? አንጃው ይቃዣል! በቴሌቪዢን ወይም በሬዲዮ ሐሳብ መግለፅን ከወያኔ መልካም ፈቃድ የሚገኝ ፀጋ
አድርጎ መዝግቦታል፡፡ አለማወቁን እንደ ዕውቀት ቆጥሮታል፡፡ ዕድል ሳይሆን መብት መሆኑን ማወቅ ተስኖታል፡፡ አንጃው በመቀጠል
ደግሞ "...በሊቀመንበርነት ሹመት..." በማለት ቀርጿል፡፡ ሊቀመንበርነት ሹመት ነው እንዴ? በፍፁም አይደለም! ሊቀመንበርነት
ሕዝብ ሲመርጥ የሚገኝ የኃላፊነት ወሰነ - ክልል መጠሪያ ነው፡፡ ሕዝብ ካልመሰለው ደግሞ ይሽራል፡፡ ሹመት አይደለም ! ሰለዚህ
እንጂነር ኃይሉ ሻውል ሹም አይደሉም ! ሌሎችም የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፖርቲ አመራር አባላት ሹሞች አይደሉም !
ሊባሉም አይገባም !አሉባልተኛው አንጃ ወረቀት ጽፎ ከመበተኑ በፊት ይህን ማወቅ እንደነበረበት ይሰማናል፡፡ ያም ሆነ ይህ ስመ
- ገናናን በአሉባልታ ለማዋረድ መሞከር በኢርቱዕ መንገድ የራስን ትንሽነት ማወጅ ይሆናል፡፡ ለዚህ ተስማሚ ብሒል እንዳለን
ደግሞ እንርሳ "የባቄላ አበባ እያደር ይቀንሣል ትንሽ ሰው ትንሽ ነው አንሶ ያሳንሣል" ይባል የለ?
ለስው በላው የወያኔ ቡድን በግልፅ የተንበረከከው የዶክተር ብርሃኑ
ነጋ አንጃ በደቡብ ኢትዮጵያ በበተነው በዚሁ እንቶ ፈንቶ በሰነቀው ፅሑñ በመቀጠል ደግሞ እንዲህ ይላል፡፡
ይህ
ሁሉ እንግልት፣ ሞት፣እሥራትና ስደት የተከሰተው እርስዎ
በሰጡት አመራር ምክንያት መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ እንደ
ዕውነቱ ከሆነ፣ የቅንጅት ደጋፊዎች ለዚህ መስዋዕትነት የተዳረጉት
ለግለሰቦች ልዕልና ሳይሆን ለአገራቸውና ቅንጅት ለያዘው ዓላማ
መሆኑን ደግመን ደጋግመን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
የራሱ የሆነ ግልፅ የፖለቲካ አቅጣጫና የርዕዩተ-ዓለም ትጥቅ
ሳይኖረው ከወያኔ ጋር ተስማምቶ መኖርን ብቻ ዐቢይ ዓላማው አድርጎ በመንፈስ ልልነት የትግራይን ሕዝብ ይቅርታ የጠየቀው
የዶክተር ብርሃኑ አንጃ በሰለጠነ አስተሳሰብ ሕዝብ ከመንግሥት በላይ ሥልጣን ያለው መሆኑን እንኳን ለመገንዘብ የሚያስችል
የዕውቀት ሰንቅ ሲያጣ ይስተዋላል፡፡ ወያኔን መከታ አድርጎ የተነሣሣው ይህ ከሐዲ የአንጃ ቡድን በእርግጥ ላይገባው ይችላል፡፡
ሆኖም ሕዝብ የተንገላታው፣ የተገደለው፣ የታሰረውና የተሰደደው ድምፁን ሰለተቀማ መሆኑን ሕሊና ያለው ሁሉ ይረዳዋል፡፡ በደረቅ
ጥላቻ የዕውነትን ፈር መልቀቅ ደግሞ ተገቢ አይደለም፡፡ አንድ ጊዜ ለመቁረጥ አስሬ መለካት ያስፈልጋል፡፡ አለማስብን ለማሰብ
በራሱ አስተውሎት ይጠይቃል፡፡ ማመዛዘን ያሻል፡፡ ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ ሁኔታ ለጠፋው የሰው ሕይወት እንዲሁም ለወደመው
ንብረት ሁሉ ተጠያቂው ማነው? ለዚህ ጥያቄ ሕሊና ያለው ማንም ሰው ተገቢ መልስ ሊሰጠው ይችላል፡፡
ዛሬ ዓለም የዴሞክራሲ መርህ አቅጣጫን መርጧል፡፡ ሰለዚህ መንግሥት
ማቋቋምና ማስወገድ የሕዝብ መብት ሆኗል፡፡ ሕዝብ ተቃውሞውን በልዩ ልዩ መንገዶች የማሰማት መብት አለው፡፡ ተቃውሞውን ለመግለፅ
ማንንም ማስፈቀድ የለበትም፡፡ ለሰላማዊ አመፅ ፈቃድ አያሻምና፡፡ አደባባይ መውጣት መብት ነው፡፡ እንዲሁም ተቃውሞን ለመግለፅ
የእግር ጉዞ ይደረጋል፡፡ ሠራተኞች ደግሞ በማምረቻ ድርጅቶች ውስጥ ከአቅም ያነሰ በመሥራት በመንግሥት ላይ ተፅእኖ የማድረግ
መብት አላቸው፡፡ በመንግሥት ተሽከርካሪዎች አለመጠቀም በራሱ መብት መሆኑን አንጣ፡፡ ሥራ በማቆም እቤት ተቀምጦ መዋልም
የሰላማዊ ተቃውሞ አካል ሆኖ ይወሰዳል፡፡ ይህን ማድረግ ወንጀል አይደለም፡፡ ምግብ የማቆም አድማም ይበረታታል፡፡ ሰላማዊ አመፅ
ለሕዝብ ሰፊ መብት ያጎናፅፋል፡፡ የአገዛዙን ደጋፊዎች ከማህበራዊ ኑሮ ማግለል በራሱ ሰላማዊ የፖለቲካ ተቃውሞ አካል መሆኑንም
አንዘንጋ፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ትምህርታቸውን የማቆም መብት አላቸው፡፡ ተማሪዎች መንግሥትን ለመቃወም የማንንም ፈቃድ
የመጠየቅ ግዴታ የለባቸውም፡፡ የአይሮኘላን ነጂዎች የመኪና አሽከርካሪዎች፣አራሾችና የመሳሰሉት ሁሉ በአገዛዙ ላይ በሰላማዊ
መንገድ የማመፅ መብት እንዳላቸው ልናውቅ ይገባል፡፡ በሰላማዊ አመጽ ደም አይፈስም፡፡ ሕይወት አይቀጠፍም፡፡ የሰላማዊ አመፅ
ዓላማ ሰዎችን ሳይሆን መንግሥትን መግደል ነውና፡፡ መንግሥት ይሞታል፡፡ መንግሥት ይተካል፡፡
የኢትዮጰያ ሕዝብ የግንቦት 97 ዓ/ም ምርጫ እንደተጭበረበረ
ተቃውሞውን በሰላማዊ መንገድ ለመግለፅ ተንቀሳቅሷል፡፡ ነገር ግን በአምባገነኖች በከፍተኛ ደረጃ ጭፍጨፋ ተካሔዶበታል፡፡
እንኳንስ ውጭ ሆነው ንፁሕ አየርና የፀሐይ ብርሃን ያገኙ የነበሩ ቀርቶ በቃሊቲ ወህኒ ቤት በእሥር ላይ የነበሩትም
ተጨፍጭፈዋል፡፡ ለዚህ ግፍ ታዲያ ከአገዛዙ ባለሥልጣናት ሌላ ማን ተጠያቂ ሊሆን ይችላል? የዶክተር ብርሃኑ አንጃ ይህን ዕውነታ
መቀበል እንዴት ተሳነው? አንጃው በዕውነተኛ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፖርቲ አመራር አባላት ላይ ግልፅ የጥላቻ አቋም
ይዟል፡፡
በዚህ ምክንያት ዕውነትን በዕውነት ሰለ ዕውነት ለማስተናገድ ፈቃደኛ
አይደለም፡፡ ሆነም ቀረ ከግንቦቱ 97 ዓ/ም ምርጫ ጋር በተያያዘ ለጠፋው የሰው ሕይወትና ለወደመው ንብረት ሰው በላው የኢትዮጵያ
የወያኔ አገዛዝ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ለወያኔ ወድዶና ፈቅዶ በሎሌነት ይዘት የፖለቲካ እሽክርናን ያፀደቀው የዶክተር ብርሃኑ ነጋ
አንጃ ይህንን ሐቅ እየመረረውም ቢሆን አንጋጥጦ ሊውጠው ይገባል፡፡
ተንበርክኮ ለወያኔ እጁን የሰጠው የዶክተር ብርሃኑ ነጋ አንጃ
ከተመስገን ዘውዴ ሐሞተ ቢስ ቡድን ጋር ውህደት መፍጠሩ ተነግሮለታል፡፡ በተዛመደ መልኩ አዲስ የወያኔ አጋር ፖርቲ ለመፍጠር
ከጅሏል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከወያኔ ሹሞች ጋር ብዙ ተሞዳሙዷል፡፡ እንደ ነፍሰ ገዳዩ ቃየል ተቅበዝብዟል፡፡ እንደ ጉረኛው ጎልያድ
ፎክሯል ፡፡ ሕዝቡን ለማሳሳት ይሯሯጣል፡፡ ኘሮፎሰር መስፍን ወልደ ማርያም ደግሞ አንጃውን በተከታታይ ምክር ይመግቡታል፡፡
በየወቅቱ ሐሳብ ይሰጡታል፡፡ ለሕዝብና ለታሪክ ከሚበጀው ይልቅ በጠባብ ቡድናዊ አቋም በተግባር የቀስተ ደመና ማዕከል ሆነዋል፡፡
ለቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፖርቲ ትንሣኤ ከመታገል ይልቅ ከአንጀኞች ጎራ ሻማ ይዘው ቆመዋል፡፡ እንዲያውም በአንጀኞች
ታሳቢ ፖርቲ ለሥራ አስፈጻሚ አባልነት በተስፋ ከተስፋ ሠነድ ላይ ስማቸውን አስቀርፀዋል፡፡ ግን ወዴት እንደሚሔዱ አውቀውና
አስበው የሚሔዱ ከሆነ በምርጫቸው የዘሩትን ወቅቱ ሲደርስ የሚያጭዱት ይሆናል፡፡ በግንዛቤ ጉድለትና ከግላቸው በሠረፀ ድክመት
የሚጓዙ ከሆነ ከአንጃው ጋር በማህበር ፀፀት ይጠብቃቸዋል፡፡
አንጃው ሰሞኑን በደቡብ ኢትዮጰያ መጠነኛ እንቅስቃሴ አድርጎ ነበር፡፡
ነገር ግን በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ በተለይ በወላይታ ጉዞው ከስሯል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በብርቱካን ሚደቅሣ
የተመራውና ግዛቸው ሽፈራው ጭምር የሚገኝበት የአንጀኞች መልዕክተኛ በጥር 8 ቀን 2ዐዐዐ ዓ/ም ወደ ወላይታ ገባ፡፡ ነገር ግን
በቀን ስብሰባ ለማካሔድ ሰለ ፈራ ማታ በአንዲት የኤዴፖ-መድህን አባል በነበረች ሴት ቤት ስብሰባውን ለማካሔድ ወሰነ፡፡
ተሰብሳቢዎችን ለማግኘት ግን አልቻለም፡፡ ሰለሆነም በደላላ ሰው ማፈላለግ ነበረበት፡፡ ብዙ ደክሞ ጥቂት ሰዎች ግን አላጣም፡፡
በተወሰነው ቦታና ሰዓት ስብሰባው ቀጠለ፡፡ ነገር ግን የአንጃው ልዑካን ቀንና ዓመተ ምሕረት እንዲሁም ርዕሰ ጉዳዩ
ባልተቀረፀበት ወረቀት ላይ ተሰብሳቢዎቹን እንዲፈርሙበት ጠየቁ፡፡ በዚህ ወቅት የአንጃው ልዑካን ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠማቸው፡፡
ምክንያቱም ተሰብሳቢዎቹ ከእነሱ ዓላማ ጋር የሚሄዱ አልነበሩምና፡፡
ሰለዚህ አዘጋጅተው ባቀረቡት ሰነድ ላይ ለመፈረም ፈቃደኛ ሆነው
አልተገኙም፡፡ ሰዎቹ ለአንጀኞቹ በመሣሪያነት ሊያገለግሉ እንደሚችሉ እምነት የተጣለባቸው ቢሆንም በተቃራኒ አቋም የተቃውሞ ድምፅ
አሰሙ፡፡ አንጀኞች ያልጠበቁት ችግር ገጠማቸው፡፡ በልዩ ልዩ የማታለያ ስልት ሐሳባቸውን እንዲቀይሩ ለማድረግ የአንጃው ልዑካን
በብርቱ ሞክረዋል፡፡ ሰዎቹ ግን ሐሳባቸውን አልቀየሩም፡፡ ሆኖም አንጀኞቹ ተስፋቸውን አልቆረጡም፡፡ ተስፋ ባጡበት በተስፋ
ገንዘብ እያወጡ ማደል ጀመሩ፡፡ በዚህም መሠረት ለአንድ ደካማ ግለሰብ ሶስት ሺህ ብር የሰጡ ሲሆን ለተቀሩት ጥቂት ሰዎች ደግሞ
ለእያንዳንዳቸው አምስት መቶ ብር በነፍስ ወከፍ ለግሰዋል፡፡ ሰዎቹ ግን ገንዘቡን ተቀብለው ወደ ቤታቸው ከመግባታቸው በስተቀር
የአንጃውን ተልዕኮ ለማሳካት አንዳችም ተግባራዊ እንቅስቃሴ አላደረጉም፡፡ እንዲያውም አንገታቸውን ደፍተው ተቀምጠዋል፡፡
የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፖርቲ አባላትና አካላት
ተጠናክረው በሚገኙበት በወላይታ ዞን የአንጃው ተልዕኮ እንደማይሳካ አውቀዋል፡፡ ተስፋቸውን ቆርጠዋል፡፡ የአንጃው ምኞት መና
ሆኗል፡፡ እን ደጉም በንኗል፡፡ እንደ አቧራ ተንኗል፡፡ በወላይታ ዞን፡፡
የልዑካን ቡድን አባላት በመቀጠል ደግሞ ወደ ጎፋ ልዩ ዞን አምርተዋል፡፡
በጎፋ ዋና ከተማ ሳውላ ውስጥ በ4/5/2ዐዐዐ ዓ/ም በቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፖርቲ አባላት መደበኛ ሰብሰባ ላይ ተገኝታ
ብርቱካን ሚደቅሣ "ኢንጅነር ኃይሉ ሻውልን ሰዎች ይጠሏቸዋል፡፡ ሆኖም አሁንም የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፖርቲ
ኘሬዝዳንት እሳቸው ናቸው! " በማለት መሠሪ ንግግር አሰምታለች፡፡ የጥላቻና የስሜታዊነት አቋሟን በአደባባይ አንፀባረቀች፡፡
ያለ አንዳች መረጃ ስም የማጥፋት ተልዕኳዋን አወጀት፡፡ ያለ ጥናት ስሜቷን አንብባ ማንነቷን አስነበበች፡፡ በአሉባልታ ፖለቲካዋ
ተገመተች ! አልጋ ላይ ሲሏት ዐመዱን መረጠች !ያሳፍራል ! ፀረ አንድነት ተልዕኮዋን በአንደበቷ መሰከረች፡፡ ግለሰብ ላይ
አነጣጠረች፡፡ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ የሰጣትን የቤት ሥራ ሰራች፡፡ በሣውላ ላይ፡፡
የአንጃው አባላት በመቀጠል ወደ አርባ ምንጭ ሔደዋል፡፡ በአርባ
ምንጭም ደካሞችን በመሣሪያነት ለመጠቀም ጥረት አድርገዋል፡፡ ወኔ የከዳቸውን ሲፈልጉና ሲያፈላልጉ ውለዋል፡፡ ነገር ግን እንደ
ልማዳቸው ገንዘባቸውን በትነው በአልቦ ውጤት ተመልሰዋል፡፡ ሰለዚህ ዛሬ በደቡብ ኢትዩጵያ ውስጥ ትርጉም ያለውን የፖለቲካ
እንቅስቃሴ የሚያደርግ ተቃዋሚ በኢንጂነር ኀይሉ ሻውል የሚመራው የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፖርቲ ብቻ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በመሆኑም የአንጃው ዓላማ ሕዝባዊ መሠረት አጥቷል፡፡ ሆኖም አንጃው ለሀገር አንድነት፣ለሰላም፣ለዴሞክራሲና ለጋራ ብልፅግና
ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡትን ዕውነተኛ የኢትዮጰያ ልጆች ስም በማጥፋት ዘመቻው ቀጥሎበታል፡፡ " ሁሉም በየፊናው ይሔድ!"
የሚለውን የዶክተር ብርሃኑ ነጋን ትዕዛዝ መነሻ አድርገ የማንቀሰቀሰው ይህ አንጃ መሞቱ ላይቀር ላለመሞት ይንጨረጨራል፡፡
ዕገዳውን ጥሷል፡፡ ሕገ ደንቡን ረግጧል፡፡ ሆኖም አሁንም ሰለቅንጅት ያላዝናል፡፡ ብቻውን ላለመሞት ሰው ፍለጋ ይባዝናል፡፡
ከወያኔ ጫማ ሥር ተኝቶ ሰለዴሞክራሲ ያወራል፡፡ ያም ሆነ ይ ዓላማው አይሳካለትም፡፡ ሕዝብ ያሸንፋል ዕውነተግ የኡትዮጰያ ልጆች
ከድል ሰገነት ላይ ይቆማሉ፡፡ የአንጃው ተልዕኮ ያለ ጥርጥር ይከሽፋል፡፡ ! ! !
?? ! !
|