|
Saturday, 09 February 2008 |
|
ፍጥምጥም?
የብርቱካን ሚዴቅሳ ቅንጅት ከተመስገን
አንጃ ጋር፤
ኢትዮጵያ ዛሬ-- ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ከአዲስ አበባው መንግስት ጋር ለመቀራረብ በሞከሩ ቁጥር ከሕዝብ ጋር ሆድና ጀርባ ከሚያደርጋቸው ማጥ ውሰጥም እየገቡ ናቸው። ዛሬ ዛሬ <ረጋ በይ> ለሚላቸው ተቺዎቻቸው ብቻ ሳይሆን ይደግፉዋቸው የነበሩትና አሜሪካ ድረስ አብረው የተጉዋዙዋቸው ሳይቀሩ የያዙት አቅጣጫ እንዳስፈራቸው መግለጥ ጀምረዋል። ግለሰብዋን በይድረስ ይድረስ ለተቁመዋቁመው ቅንጅት <ቀስተ ደመናን> ወክለው ይቀመጡ ዘንድ ያመጡዋቸው ዶ/ር ብርሃኑን ጨምሮ <እኔ አላማረኝም> ያሰኘ ሂደት ውስጥ መዋኘት ጀምረዋል- ወ/ሪት ብርቱካን። አንዳንዶች ግን የዶ/ር ብርሃኑና የወ/ሪቱዋ የአደባባይ ልዩነት <ስልት> ነው ይላሉ።
ሰሞነኛ ሆኖ እዚህ አዲስ አበባን እያነጋገረ ያለው ወ/ሪት ብርቱካን መሰረታዊውን የቅንጅት ውሳኔን አሌ ብለው ከይስሙላው የገዢው <ሸንጎ> ከተቀላቀሉትና <ቅንጅት እኔ ነኝ> ከሚሉት አቶ ተመስገን ጋር <ተዋሀድን> የሚለው ይፋ ግርግር ነው። በዚህ ሁለቱ የቅንጅት <አንጃዎች> ጋብቻ <ከጀርባ> ሆነው ለመዘወር ዕድል አጋጠሙዋቸዋል የሚባሉት ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያምን የተጫወቱት ከፍተኛ ሚና ስለመሆኑ ምንጮቻችን መስክረዋል። ከቀስተ ደመና በራሳቸው ፈቃድ መልቀቂያ ጠይቀው ተሰናበተው የነበሩት ፕሮፌሰሩ ከቶም በአዲስ ምርጫ <የላዕላይ ምክር ቤት> አባል ሆነው ተመረጡ መባሉ ብዙዎችን ግር አሰኝቶዋል። አንዳንድ ምንጮች ኢንጂነር ሀይሉና ዶ/ር ብርሀኑ ላይ ያነጣጠረ ትችት በሰነዘሩበት ጊዜ <ብርቱካን ትምራ> ማለታቸውን አስታውሰው፤ ያ ጉትጎታቸው እንደልባቸው የሚዘውሩዋት <ሌጣ ሰው> ከማግኘታቸው ጋር ያያየዙባቸው ሞልተዋል። ወ/ሪት ብርቱካን ከትኩስ ስሜታቸው ውጭ ብዙም ጥልቀት እንዴላቸው የሚገልጡ፤ ቀደም ሲል በዶ/ር ብርሃኑ አሁን ደግሞ በፕሮፌሰር መስፍን ይመራሉ መባላቸውን አለጥርጥር ይቀበሉታል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወ/ሪት ብረቱካን <ህጋዊ>ና ብዙዎች የልመና ትግል የሚሉትን የፕሮፌሰር መስፍን አቅጣጫን የመረጡት በዚሁ የተነሳ እንደሆነ በማስረጃነት አቅርበው ከቀደሙት የወ/ሪቱዋ አገላለጥ ጋር መቃረኑን በማስረጃነት ያነሳሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ምስጢራዊ ምንጮች ዶ/ር ያዕቆብ ወ/ማርያም የ<ብርቱካን ቅንጅት> አንጃን ለመምራት ከወዲሁ ውስጥ ውስጡን የማግባባት ስራቸውን እንዳጠናቀቁ መግለጥ ጀምረዋል። በአሜሪካ ለረዥም ጊዜ የኖሩትና በአሜሪካው ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ከቅንጅት አመራር አባላት መካከል <አፍቃሪ አሜሪካ> ተደርገው በዋነኛነት የሚጠቀሱት ዶ/ር ያዕቆብ Intellectual At Risk በተሰኘ ድርጅት የተቸረውን የስራ እድልም ሳይቀበሉ መቅረታቸው ከዚህ ህልማቸው ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተነግሩዋል።
ወ/ሪት ብርቱካን ብዙዎችንና በተለይም ደጋፊዎቻቸውን በሚገፋውና በሚያባርረው አዲስ አቅጣጫቸው እንዲገፉብት ዶ/ር ያዕቆብ ከፕሮፌሰር መስፍን ጋር ከጀርባ መሆናቸውም ሲታወቅ የተቃውሞ እሳቱን ወ/ሪቱዋ ከተቀበሉ በሁዋላ ብቅ የማለታቸው ምስጢር የሚከሰት ይሆናል። ቅንጅቱ ባለስምንት ነጥቦችን አቅርቦ በነበረበትና ሰላማዊ ትግሉ በተጋጋመበት ወቅት ተነጥለው ለወያኔ ይሁንታ በመስጠት የህዝብ ግንኙነት ሽፋን ሀነው ያገለገሉት የእነአቶ ተመስገን ቡድን አባላትን ተቀብለው ወ/ሪት ብርቱካን <ጋብቻ> ለመፈጸም መብቃታቸው የተለፋውና የተከፈለው መስዋዕትነት ከንቱ እንዳደረገው በምሬት የሚናገሩ ወገኖች በርክተዋል። ከወህኒ ለመፈታት ጥፋተኞች ነን ብለው የወጡብት ሁኔታ አሳዝኖ ሳያበቃ ከዚህ መሰል ቀጥተኛ ክህደት ጋር መያያዙ ወ/ሪት ብርቱካን ትግሉን ከፍትሀና ከዲሞክራሲ ጥያቄ አውጥተው ለግል የመቀመጫ ውድድር ሊያደርጉት እንደሆነ ያደረባቸውን ስጋት የሚገልጡም አሉ። ወ/ሪት ብርቱካን ከተመስገን ቅንጅት አንጃ ጋር መጋባታቸው ብቻ ሳይሆን አጠያያቂ የሆነው ለህወሀት መንግስት በ<ሽምግልና> ስም ድለላ ለያዙት ፕ/ር ኤፍሬም ይሰሀቅ የላኩት የአቤቱታ መልዕክት ነው። ሰፋ ያለ ዝርዝር ወደፊት የምናቀርብበት ቢሆንም የመለሰ መንግስት በወ/ሪት ብርቱካን በእጅ አዙር ቀረበለት ለተባለው የ<እንነጋገር> ጥያቄ ከሁሉ አስቀድሞ በውጭ በኢትዮጵያውያን ጥረት ለአሜሪካ መንግስት የቀረበውን የህግ ረቂቅ ኤች አር 2003 በይፋ እንዲያወግዙ ተጠይቀዋል። ወ/ሪቱዋ በባህር ማዶ ያሉትን ወዳጆቻቸውን በማለሳለሱ ከወዲሁ ሙከራ ለማድረግ እየሞከሩ መሆናቸው ሲታወቅ አዳጋች ሳይሆንባቸው እንዳልቀረ ተገምቱዋል። <ተገድጄ ለድርጅቱ ህጋዊነት ስል ማውገዝ ግድ ሆኖብኛል> የሚል መከራከሪያን ይዘው ለመነሳትም ይሞክራሉ ተብሉዋል። ርግጥ ነው ወ/ሪት ብርቱካን ለገዢው ፓርቲ በ<ሽማግሌዎቹ> አድራሽነት <እንነጋግር> ባሉበት ደብዳቤያቸው ቀደም ሲል በአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት ምስክርነት ለመስጠት በተገኙ ጊዜ የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር መገኘትና ስለገዛ ምስክርነታቸው የተለሳለሰ ማብራሪያ ለመስጠት ከጅለዋል። የኦብነግ በአሜሪካው ምክር ቤት ምስክርነት ላይ ከርሳቸው ጋር መገኘት አጋጣሚ መሆኑን ሲናገሩ <ትብብር ለነጻነትና ለዲሞክረሲ> የተሰኘውን አራት ድርጅቶች ጥምረት <አናውቀውም!> ብለዋል በዚሁ ደብዳቤያቸው። ወ/ሪቱዋ በዚህ አቅዋማቸው በውጭ ቃፊር ሆነው ሲያገለግሉዋቸውና ሲያደራጁላቸው የነበሩትን የእነ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ድጋፍ <ቢቀርብኝ ይሻላል> የሚሉም አስመስሉዋቸዋል።
ወ/ሪት ብርቱካን በቅርቡ ወደ አሜሪካ እንደሚመጡ መረጃዎች የተገኙ ቢሆንም ቀደም ሲል ከወህኒ መፈታታቸው ጋር በልዑክነት በመጡበት ጊዜ በድርጅታዊ ስራ አሜሪካንን ይዘውላቸው ከነበሩት ከእነአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጋር በተፈጠረው መቃቃር የመጪውን አሜሪካ ቆይታ እሾሀማ ያደርግባቸዋል። አቶ አንዳርጋቸው ወ/ሪት ብርቱካን የቅንጅትን (የድርጅቱን) ስም ለመቀየርም ሆነ የያዙት አቅጣጫን <ልመና> ሲሉ ያጣጣሉብት ጽሁፍም በተለያዩ ድረ ገፆች ተተነቡዋል።
ወ/ሪት ብርቱካን ወደ አሜሪካ የመምጣታቸው ዜና ከውጭ ድጋፍ ቅርንጫፎቻቸው ጋር ለመምከርና በተለይም የሰሜን አሜሪካው አዲስ አመራር ከመረጠ በሁዋላ ቡራኬ ለመስጠት በሚል ነው። ይሁንና ከድጋፍ ድርጅቶቹ ቅርብ የሆኑ እንደሚሉት አዲሱና የ<ልመና> የተሰኘው ወ/ሪት ብርቱካን አካሄድ እንደቀድሞው ገንዘብ ከዲያስፖራው አያስገኝም ከሚል ስጋት ተዘፍቀዋል። በውስጥ ለውሰጥ ቅርብ ናቸው ለሚባሉ <ምስጢር> እየተባለ በህቡዕ ሌላ ወሳኝ ትግል ይካሄዳል የሚል ተስፋ እየተሰጣቸው መሆኑ ተደርሶበታል።
የኢትዮጵያ ዛሬ ዜና ምንጮች በውጭ የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ ከገዢው ፓርቲ ጋር ከተቻለ ለማስታረቅ በሚል ደግሞ በዲያስፖራ ከሚገኙት የወ/ሪት ብርቱካን ደጋፊዎች የተውጣጣ አንድ ልዑካን ቡድን ከአሜሪካ ወደ ፕ/ር ኤፍሬም ይስሀቅ፤ አዲስ አበባ ጉዞ እንደሚያደርግ ተሰምቱዋል። በዚህ ዝርዝር ውስጥ የተጠቃለሉትን ወደፊት የምንገልጥ ቢሆንም ከዋሽንግተን ዶ/ር ሞገስ ገብረ ማርያም እንዳሉበት ታውቁዋል። ዶ/ር ሞገስ ቀደም ሲል የቅንጅት አመራር አባላት በወህኒ በነበሩብት ጊዜ በሰሜን አሜሪካ የቅንጅት ፖለቲካ አመራር አባል የነበሩና ከፕ/ር ኤፍሬም ይስሀቅ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ያላቸው በመሪዎቹ የ<ይቅርታ ደብዳቤ> መፈረም ዙሪያ ዋነኛ አገናኝ የነበሩ ግለሰብ ናቸው።
የደበበ እሸቱ መጽሀፍ ከቀስተ ደመና እስከ ወህኒ
ኢትዮጵያ ዛሬ በምድረ አሜሪካ የወ/ሪት ብርቱካንን አንጃ ወክሎ ለ<ደፋር ተሳዳቢነት> በዘመቻ መልክ የተላከ የሚመስለው ተውኔተኛው ደበበ እሸቱ ከ<ቀስተ ዳመና እስከ እስር ቤት> በሚል ርዕስ መጽሀፍ ለማሳተም የገንዘብ እርዳታ እየተማጸነ መሆኑ ተደረሰበት። ገፁ በዛ ያለው የ<ቲያትረኛው> ደበበ መፅሀፍ <እኔ> በሚል ስንክሳር የተጨናነቀ መሆኑን ምንጮቻችን ደርሰውበታል።
ጊዜያዊውን የአሜሪካ መኖሪያ ዋሽንግተን አካባቢ ከአርቲስት ዓለም ፀሀይ ወዳጆ ቤት ያደረገው ደበበ እሸቱ፤ ኢንጂነር ሀይሉ ሻወል ስብሰባ ሊያካሂዱ ባቀዱብት የአሜረካ ክፍለ ከተሞች ሁሉ እየተጉዋዘ ቀድሞ የስብሰባ ጥሪ በማስደረግ የሊቀ መንበሩ ስብሰባ እንዲከሽፍ ለማድረግ ሲሞክር ሰንብቱዋል። ተውኔተኛው ደበበ በደረሰባቸው ቦታዎች በጸያፍ አነጋገሩ የተነሳ ደጋፊዎቹን ሳይቀር እያሳፈረ መምጣቱን ለመረዳትም ችለናል። ደበበን በቅርብ የሚያውቁትና መዋሸት ሁለተኛ ተፈጥሮው ነው የሚሉ፤ በቀስተ ደመና ውስጥ የነበረው ተሳትፎ እጅግም እንደሆነ አበክረው ሲገልጡ፤ የሌሎችንም ታሪክ ለመቀማት ወደ ሁዋላ የሚል ተፈጥሮ እንደሌለው ይናገራሉ። መፅሀፉም ይህንኑ የሚያረጋግጥ እንደሚሆን ይገመታል።
|