|
የተስፋ መቁረጥ መድሀኒቱ ተግባር ነው-ክንፈ ሚካዔል |
|
|
|
Tuesday, 13 May 2008 |
(Action is the antidote to despair, John Baez)
ይህ አባባል ዛሬ እኛ ኢትዮጵያውያን ለምንገኝበት ሁኔታ ገላጭ እና መሪ ምሳሌ ነው። በደረሰብን "ሽንፈት" ሆነ የርስ በርስ ግጭት ያለንበት ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ በመሆኑ ወደየራሳችን ፊትችንን መልሰን ወይም ወደ ሚመቸን አካባቢ በመንሰራፋት ሁሉን እርግፍ አድርገን የተቀመጥን ወይም የመረጥን ሰዎች ሆነናል። ይህ ደሞ ከድጡ ወደ ማጡ ገባን እንጂ የተሻለ ላይ አልወደቅንም። ምክንያቱም የትም ብንደበቅ ችግራችን ካጠገባችን አይጠፋምና፤ የትም ብንሄድ ይከተለናል። ኢትዮጵያዊነታችንን ለመለወጥ ብንሞክር ጭራሽ የመለያ/የማንነት ቀውስ ውስጥ ወድቀን መልሰን ለመቆም ብዙ ይፈጅብናል። በምንችለው ችግሩን ፊት ለፊት ብንቋቋመው ለትግሉ ከምናደርገው አስተዋዖ በስተቀር በራሳችን ላይ የመተማመኑ ዕምነት ከፍ ይላል።
ጎልቶ አይላ (The Third Blow, May 7, 2008) ሶስተኛው በደል በሚል ባወጣው መጣጥፉ ሁለተኛውና ሶስተኛው በደል የደረሰው ከሰነ መንግስት ፓርቲ መሪዎች የርስ በርስ ሽኩቻ ያስከተለው የቁጣና የተስፋ መቁረጥ ዝንባሌ ስቃዩ የከፋና የሚያስከትለውም ችግር ረዘም ያለ ጊዜ የሚፈጅ እና በዚያው መጠን አገሪቱ እየጠፋች እንደሆነ ነው። ለዚህም ሁላችንም ተጠያቂ እንደሆን እና ከዚህ ማምለጥ እንደማንችል ነው። አንተ ነህ/ሽ ብንባባል ዋጋ የለውም።
ከየት እንጀምር? ኩችዬ ችግሩ የማናጅመንት ነው ወዳጄ! በሚለው የሚያዚያ መጣጥፉ ያቀረባቸው ዝርዝሮች እንዳሉ ሆነው በበኩሌ ከዚያ በፊት መቅደም አለባቸው የምለው ሁለት ነገሮች የሚከተሉት ናቸው።
በመጀመሪያ ሁላችንም ያገባናል የምንል ኢትዮጵያውያን እጅ ለጅ መይያዝ አለብን እላላሁ። ይህ ደሞ ካለፈው ጀምሮ የተሰራውን ስህተት ማን ተጠያቂ እንደሆነ፣ ለምን ስህተቱ እንደተፈጸመ ሁሉም ያደረሰውን በደል ሆነ የደረሰበትን ድርሻውን እያነሳ በይቅርታ ተላልፈን ሁለተኛ ቁርሾውን ያነሳ ቁርሾውን ተባብለን ባዲስ መጀመር አለብን ነው። ከዚህ በኋላ የወደፊቱን ዕቅድ አንድ ላይ በመንደፍ ፍልሚያውን ብንጀምር ዕውነትም በዕርግጠኝነት ወያኔን መታገል በትክክለኛ ትርጉሙ ተያያዝነው ማለት ነው። አለያ እስከ አሁን እንደሚደረገው የህዝብ ቁጣ ገንፍሎ በሚነሳው አመጽ ሳቢያ ሁሉም ከእንቅልፉ እየባነነ አለሁ ያዙኝ ልቀቁኝ ቢል ይህ ገበር (ፓሽን) እንጂ ያገር ፍቅር አይዶለም። ገበር ደሞ እንደ ተወርዋሪ ኮከብ ብልጭ ብሎ ቶሎ ዕልም የሚል ስሜት ስለሆነ በኢንምንት ያልፍና እንደገና ወደ እንቅልፋችን ነው። ያ የቅርብ ሩቁ የ66 ግብታዊነት ዛሬም ከሶስት አስርታት በኋላ አለቃችሁ ብሎናል።
ሁለተኛው ገና ሲጀመር ጥርት ያለ መስመር እንዲይዝ ማድረግ ትልቁ ስራ ነው። ሰለዚህ መጀመሪያ እጅ ለእጅ መያያዝ ያለበት አገሬ ወገኔ የሚለው ኢትዮጵያዊ ያገሩን ሎአላዊነት፣ ህበረ ብሄርነቷን፣ ዳር ድንበሯን ወያኔ ያስገነጠለውም ይሁን ማስገንጠል የሚፈልገውን ጨምሮ ባቅም ማጣት ምክንያት ያውሮፓ ቅኝ ግዢዎች ከልለው የሰጡን ድንበር እንዳለ መጠበቅ አለበት የሚለው ክፍል ነው። ማንም ከቤቱ ጀምሮ ነው ወደ ውጭ የሚዘልቀው። ቴዌድሮስ ከጎንደር፣ ዮሐንስ ከትግራይ፣ ሚኒሊክ ከሸዋ ጀምረው ነው የተሰለፉት የገነቡት። ጠቅላላው ያለም ታሪክ ከዚህ የተለየ ትረካ የለውም። በ66 እንዳየነው ሁሉም ሀ/ሥሴን ለመጣል ባንድ ይሰለፍ እንጂ እያደር የሁሉም አጀንዳ እንደ ስማቸው የተለያየ መሆኑ ኋላ የወጣ ጉድ ነው። ስለዚህ ካሁኑ ወገን እና ጠላትን ለይቶ መሰለፍ ወደኋላ ከሚያስከትለው ዝርክርክነት ከመጠበቁም በላይ ይበልጥ ሊደርስ ከሚችለው የከፋ ገዳፋ ያድናል። ተዘጋጅተን መጠበቅ አንዱ አስቀድመን ማቀድ ያለብን አበይት ጉዳይ ነው። እንደ ምሳሌ ባለፈው ሳምንት እዚህ ሜልበርን አንድ የወያኔ የፍርድ ሚኒስቴር የተማረበት የሜልበርን ዩኒቨርሲቲ የህግ ፋካልቲ ባዘጋጀው (ዕርግጠኛ አይደለሁም ማን እንዳዘጋጀው ግን ጥሪው ከህግ ፋካልቲው ነው) ሴሚናር ላይ እንደ ቀድሞ ተማሪያቸውም እንደ ባለስልጣንነቱም ለህግ ተማሪው ገለጻ እንደሚያደርግ ዲፓትትሜንቱ መጋበዙን በራሱ ዌብ ገጽ እና በማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ማሳወቁ በቋጠሮ ድህረ ገጽ ላይ ተነቦ ነበር። ይህ ድንገት የመጣ በመሆኑ ዝግጅት ለማድረግም ሆነ ቦታው ለመገኘት ስላልተቻለ/ስላልተደረገ ተላኪው ሚኒስቴር ያለምንም ተቃውሞ የመጣበትን ተልዕኮ ለመፈጸም ችሏል። ባንጻሩ ቀደም ብሎ የተሰማው በካውንስለሩ በግራም በኩል የተዘጋጀው እና የተጠራው ግን ሊከሽፍ ችሏል ለምን በቂ የመዘጋጃ ጊዜ ስለነበረ ብዙ ሰው ለመተባበር በመቻሉ ነው። ይህን ጉዳይ በሚመለከት ማለት ሁልጊዜ ተዘጋጅቶ መጠበቅ እንደሚያስፈል አንድ ለዚህ ዓላማ የሚውል (አድ ሆክ) ኮሚቴ መፍጠር እንደሚያስፈልግ አንድ ትንሽ ማስታወሻ ለቋጠሮ ልኬ ነበር (ማየት ለሚፈልግ እግርጌ አያያዤዋለሁ) ቆሞ ለሚያድር ጠላት ቆሞ መጠበቅ እንጂ መዘናጋቱ ለሚዘነዘረው እና ለሚቃጣው ዱላ ተመቻችቶ መጠበቅ ነው።
እስከ መቼስ መጓተተና መንጓፈፍ ያስፈልጋል ትላንት ሳናስበው እና ሳንጠብቀው የኤርትራ ምድራችን ወደ ሌላ አምባገነን እጅ ገብቷል። ሌላው መሬታችን ደሞ በድጋሚ ወደ ሌላ አምባገነን ሲዞር እንደ ልማዳችን እንደ ተረት ተረት ኢትዮጵያ ድሮ ድንበሯ ከቀይ ባህር እስከ ህንድ ውቅያኖስ ነበር ልንል ነው። ልክ ዛሬ ጥንት ጠረፋችን እስከ ሳውዲ ድረስ ነበር እንደምንለው ማለት ነው። የድሮ ዝናችን አሁን ላለንበት ምንም ጠቀሜታ የለውም። ያ ዝና አሁን ላለንበት የሚጠቅመው ተከብረን ተፈርተን አገራችንን ስንጠብቅ ብቻ ነው። ታልቁ ተስፋዬ ለማ በኦርኬስትራ ኢትዮጵያ በኩል በጥላሁን ገሠሠ ድምጽ የዛሬ 30 ዓመት እንዲህ ብለው ነበር
የድሮ ዝናሽ ላይጠቅምሽ እንዲህ ነበርኩኝ ማለትሽ፣
ይታገላል እና ሊያጠፋሽ እረ ዝም በይ እባክሽ፤ እረ ዝም በይ እባክሽ፤
ዛሬ ያለንበት የከፋ ሁኔታ አፍ የሚያሲዝ፣ አንገት የሚያስደፋ፣ የሚያሳፍር እንጂ አፍ አስከፍቶ ቁጢ የሚያሳምስ ቡፋ የሚያስነፋ አይደለም። የምንበላው የሌለን፣ ፍጹም የታረዝን፣ የለማኝ ለማኝ፣ የድሀ ድሀ፣ እንዲያው በደፈናው ያጣን የነጣን ድሆች እንጂ እንደ ሀገር የሚያስቆጥረን ምንም መስፈሪያ የለንም። ድንበር እንዳይባል መለስ ዜናዊ እንደ ግል ሀብቱ ትንሽ ትንሽ እያለ ለከበቡን ጠላቶቻችን ይቆርስላቸዋል። አንድ ብሔራዊ ቋንቋ እንዳይኖረን እና እንዳያድግ በተለያየ የተራቀቀ ዘዴ ሲኮረኩመው ይገኛል። ሀብረ ብሔርነታችን እንዳያድግና ባንድ እንዳንሰለፍ አንዱን ከሌላው የሚለየውን እያጎላ ጦር ያማዝዛል። ራስ ሳይቀና ጎተና እንዲሉ ገና በግራችን ሳንቆም ሶማሌ ውስጥ ገብቶ ገዳፋው ጥቅል ዘለቄታ ወዳለው የጎረቤት ጠብ ውስጥ ይከተናል። በቅርቡ ደሞ ለሱዳን የሰጠው መሬታችን ባካባቢው ህዝብ በጦር ቢከበርም በጓዳ ያረገው ፊርማ(የሰነድ ማስረጃ ካለ/ከተገኘ) ወደፊት ተደቅኖ ከሚጠብቀን የጎረቤት የድንበር ችግር/ግጭት ሌላው ነው። ይህ ሁላ የሆነው የሰሜኑ ግዛታችን ችግር እዳር ሳይደርስ ነው።
የሰነ መንግስት ድርጅቶች እንደ አሸን የፈሉበት ጊዜ ቢሆንም አንድ አለኝታ የሆነ ፓርቲ እስከ አሁን አልተገኘም። ቅንጅት የመጨረሻ አይሆንም በቅርብ በነብርሀኑ በኩል የሚፈጠር ሌላ ድርጅት እንዳለ ቀደም ተብሎ ተወርቷል። የዛሬ ሁለት ወር ግድም የኢትዮጵያ አንድነት መድረክ የሚል መቋቋሙን በየድሀረ ገጹ ተከትቧል። ዲሞክራሲ በድባብ ትሂድ ማንም በሚፈልገው እና በሚያምንበት መደራጀቱ ክፋት የለውም። ነገር ግን ይህ አደረጃጀት ለርስ በርስ ጠብ ከሆነ አንዱ ሌላውን ለመጥለፍ ከሆነ ፍሬ ቢስ ነው። የስካሁኑ ከዚህ የተለየ ተግባር አልታየበትም። ወደፊትም ይለወጣል የሚል ትንሽም ጭላንጭል አልፈነጠቀም። ሁሉም በየፊናው ወያኔን ቢጋፈጥ የሳት ራት እንጂ የፈየደው የለም። ይህ ሁኔታ የጋራ ጠላታችንን ለመጣል አላስቻለንም እንዲያውም የርስ በርሱን የልፊያ ዘመን አራዝሞ የትግሉን አሽቀንጥሮታል።
ማሳረጊያው ላይ የምደግመው ቢኖር ያው ከላይ እንዳስቀመጥኩት ያገሬን አንድነቷን የሚፈልጉ ሀይሎች (ሉአላዊነትን፣ ድንበሯን፣ ሀብረ ብሔርነቷን/ዝብርቅርቅነቷን ረጂም ታሪኳን ወዘተ) ሳይውሉ ሳያድሩ በጥንቃቄ ተሰብስበው አንድ አለኝታ የሆነ ፓርቲ መፍጠር ወይም ለምፍጠር ለቅድመ ዝግጅት የሚረዳ እና ቀጣዩን ስራ ለማመቻቸት የሚያስችል ደርግ (በእንግሊዝኛ ኮሚቴ ማለት ነው) ቢቋቋም ወደ ትግሉ ለመግባት ዝግጅቱ ተጠናቋል ማለት ነው።
ሌላው ይህ የምንመኘውን አንድነት ያሳጣን ያሳለፍነው የትግል ዘመን ሲሆን ችግሩና በደሉ እየተደራረበ ያሁኑ በድሮይ ላይ እየተጨመረ ላፍታ እንኳን ቆም ብለን ማድረግ ያለብንን ለማሰብ አልቻልንም። ለዚህም ነው ተስፋዬ ለማ ከሶስት አስርታት በፊት ዘንድሮ በሚለው ድርሳናቸው እንዲህ ያሉት፡ የሚገርመው ግጥሙ አሁን ህያው ነው ያለንበትንም ይገልጻል
በዚያኛው ተገርመን ጥቂት ሳንቆይ፣
የዚህኛው መባስ አያስቅም ወይ፤
የተሰውቱን ወገኖቻችንን አልቅሰን ለመቅበር የተከለልን ህዝቦች ነን የከለከለን ቢወገድም አማክሎ የገባውም በባሰ እና ጠለቅ ባለ ዘዴ ችግሩን አባብሶ ቅጥ እያሳጣው በወጉ እርማችንን ለማውጣት እንኳን ዕድል አላገኘንም። በእርስ በርሱ ጦርነት በፈጸምነው በደል ይቅርታው በመንግስት ደረጃ የሚታደም እንጂ (እንደ ደቡብ አፍሪካ ተምሳሌት) እንዲያው በየጓዳው ወይም በየግላችን የሚዳኝ አይመስለኝም። ለምን ቢሉ የክፋቱ ጥልቀ እና የጭካኔው አረመኔአዊችነት ብቻ ሳይሆን በደሉ እያንዳንዱን ቤት ስላንኳኳ ነው። ስለዚህ ዕድሜ ልካችንን ጥርስ ከማፏጨትና ከንፈር ከመምጠት ክፍ ብለን የተሰውቱን ዝንት እንድንዘክር አንድ ቀናኢ የሆነ አለኝታ ፓርቲ ፈጥረን በመታገል ነው። ለዚህ እንዴት እና ለስኬቱ ከላይ የተቀመጠው መስፈርት ለጅማሬ በቂ ነው። ስለዚህ ለተስፋ መቁረጥ ፍቱን መድሀኒቱ ተግባር ነው።
ለሜልበርን ኢትዮጵያውያን!!!
ግፍና ገፈቱ ከመጠን አልፎ በማን አለብኝነት የሚንደላቀቀው ወያኔ ዛሬ ብሎ ብሎ ወሰን አልፎ ባህር አቋርጦ አለንበት ድረስ ሊሰድቅብን ተልካሻ ተወካዮቹን እዚህ ሜልበርን መላኩን በአውስትራሊያ ሆዳም ተወካዩ በአቶ ግራም በኩል ዜናው ተሰራጭቷል። አቶ ግራም ከበረሀ ጀምሮ አብሮአቸው የተሰለፈ አስሊ የወያኔ ደጋፊ ነው። ለዚህ መስተንግዶ ቀና ደፋ ማለቱ ሊገርመን አይገባም።
አሁን የምንገኝበት የተሸናፊነት የስነ ልቡና ውዠንበር እና አጃቢው የርስ በርስ ግጭት በጥምር ለወያኔ የልብ ልብ ሰጥቶታል። ወያኔ ተቃውሞ ካልገጠመው በስተቀር የዝምታውን ተቃውሞ እንደ ፍራቻ መቁጠሩ ሰርክ የምናየው ነው። አምባገነኖች ዘጭ ብለው እስኪወድቁ ድረስ ምንም የሚፈሩት ነገር የለም። እፊት ለፊታቸው ያለውን ዕውነታ ማየት ስለማይፈልጉ ሁልጊዜ ወሬአቸው ድል በድል ነው። እንደምናስታውሰው የትላንቱ ኮምቦራም አምባገነን መንግስቱ ሀ/ማሪያም ድል በምስራቅ፣ በሰሜን፣ በደቡብ እያለ ሲዘፍን እጁ ሳይያዝ ባሜሪካ የስለላ ድርጅት አማካይነት ወደ ዚምባብዌ እንዲጠለል ሆኗል። የወያኔ ቁንጮም ከዚህ የተለየ ዕድል አይኖረውም። ህዝብ የማይደግፈው ጎዳናው የቁልቁለት ውድቀቱም ባንድ ጀንበር መከስከስ ነው።
ባለፈው ሳምንት ዕለተ ሀሙስ አንድ የወያኔ የፍርድ ሚኒስቴር በሜልበር ዩኒቨርሲቲ ሰሚናር የሰጠው ድንገት ሳናስበው እና ሳንዘጋጅ ስለሆነ ያለምንም ተቃውሞ የሚያወራውን አውሮቶ ጨርሷል። ይህ ጣፊ ማስታወቂያውን ያነበበው ሮብ ማታ በቋጠሮ ድህረ-ገጽ ነው። በዕለቱ ተስፋ ከመቁረጥና ከመብገን ሌላ ለብቻም ሆነ በጋራ እንኳን ልናደርግ ልንሞክርም አልቻልንም። እንዲህ አይነት አጋጣሚ ሊደጋገም ይችላል። ወያኔ ሌት ተቀን ሳያሰልስ እያንዳንዷን ቀዳዳ ለመድፈን ባለጋራዎቹንም ደብዛቸውን ለማጥፋት የማይፈነቅለው ደንጊያ የማጭረው መሬት የለም።
ለሜልበርን ኗሪ ለማጋራት የምፈልገው ቢኖር በኛ በኩል እንቅፋቱ ሲመታን ከመሯሯጥ በስተቀር እንደ ወታደር በተጠንቀቅ ቆመን መጠበቅ አለያም ቀደም ብለን ተዘጋጅተን ማድረግ የሚገባንን ለመፈጸም አልቻልንም። ስለዚህ ፍላቶት ያለን ሰዎች ተነሳስተን አንድ ቋሚ አስተባባሪ ደርግ (ኮሚቴ ባማርኛ ሲመለስ ደርግ ማለት ሲሆን ወታደራዊው አምባጋነን መጠሪያው መለያውም አርጎት ትርጉሙም ሱሙም ከመዝገበ ቃላታችን ተወግዷል) አቋቁመን የበኩላችንን ብንወጣ የሚጠበቅብን ነው።
ድርጅቶች ካሉ? ከየድርጅቱ ከሌሉ ፍላጎት ያለን ላገራችን እና ለወገናችን የምንቆረቆር ሰዎች ተሰባስበን ብንጀምር ላላማችን መሳካት የመጀመሪያ ዕርምጃ ነው ብዬ አምናለሁ።
የነገውን የተቃውሞ ሰልፍ ያዘጋጁትን ሰዎች እያመሰገንኩ እንዲሁ እንደተነሳሱ ከላይ የቀረበውን ሀሳብ ከዳር እንዲያደርሱት እየተማጸንኩና እያበረታታሁ ነው።
እስቲ ሁላችንም አንድነት አንድነት ብለን ተነስተን እጅ ለእጅ እንያያዝና እንጓዝ!!
ኢትዮጵያ በቆራጥ ልጆቿ ታሸንፋለች!!
ክንፈ ሚካዔል
ሜልበርን ኸታች ኸስር
ሚያዝያ 27 ቀን 2ሺህ ዓ/ም
|