|
ወዝ አደሮች ከጃዊ በግዴታ እንዲወጡ ተደረገ |
|
|
|
Friday, 23 May 2008 |
|
በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም ውስጥ በጉልበት ሥራ የሚተዳደሩ የቤንሻንጉል ተወላጆች ለብዙ ዓመታት ከኖሩበት ከጃዊ ከተማ በግዴታ ወደ ትውልድ ሠፈራቸው ሰሞኑን እንዲመለሱ መደረጉን የዓይን ምሥክሮች አመለከቱ፡፡
የምዕራብ ጎጃም የአገዛዝ አካላት ለምን የጉልበት ሠራተኞች ከጃዊ እንዲወጡ እንደሚገደዱ ተጠይቀው ሲመልሱ "ሁሉም በትውልድ ቀዬው ይሥራ!" የሚል አጭር የዘረኝነት መልስ መስጠታቸውንም የዓይን ምሥክሮች አክለው አስረድተዋል፡፡
አንዳንድ ኢትዮጵያውያን የቤንሻንጉል ተወላጆች ከጃዊ እንዲወጡ ስለመደረጋቸው በሰጡት አስተየየት "የአማራን ሕዝብ ዘረኝነት ማስተማር በፍፁም ስለማይቻል ገዥዎች በከንቱ ይደክማሉ፡፡" በማለት መናገራቸውንም ከወደ ምዕራብ ጎጃም ከደረሱን መረጃዎች ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሌላም በኩል በቤሻንጉል ክልል በመተከል ዞን በፓዌ ወረዳ በጣና በለስ ጣሊያን በሠራቸው ቤቶች ውስጥ ለብዙ ዓመታት የኖሩ ዜጎችን የወያኔ ሹማምንት ለቅቀው እንዲወጡ ማስገደዳቸውን ሰሞኑን ከውጭ ፓዌ የደረሱን መረጃዎች አመለከቱ፡፡
ባሁኑ ወቅት በዚሁ አስገዳጅ ትዕዛዝ መኖሪያቸውን ለቅቀው የወጡ አያሌ ዜጎች መጠለያ አጥተው ሜዳ ላይ የፈሰሱ ሲሆን የአገዛዙ ሹማምንት ለተፈናቃዮቹ ምንም የሠጧቸው ተስፋም እንደሌለ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዕህል ከአማራ ክልል ወደ ቤንሻንጉል እንዳይገባ የአገዛዝ አካላት በመከልከል ላይ እንደሚገኙ የዓይን ምሥክሮች ከቦታው በስልክ አስታውቀዋል፡፡
በዚህ ምክንያት ባሁኑ ወቅት በቤንሻንጉል ክልል በመተከል ዞን በፓዌ ወረዳ በከፍተኛ ደረጃ የዕህል እጥረት እንደሚታይ ለማወቅ ተችሏል፡፡
|