RSS 2.0 Email us: webmaster@mahder.com

Ethiopia: Mahder.com -Ultimate Ethiopian News and Information Portal

Saturday
Nov 22nd
Home arrow News arrow ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል በአዲስ አበባ አቀባበል ተደረገላቸው
ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል በአዲስ አበባ አቀባበል ተደረገላቸው Print E-mail
Tuesday, 03 June 2008

የቅንጅት ፓርቲ መሪ ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል በአዲስ አበባ አቀባበል ተደረገላቸው

      በ1997 ዓ.ም ብሔራዊ ምርጫ ውድድር ላይ የኢሕአዴግን ፓርቲ በሕዝብ የዴሞክራሲ የድጋፍ ድምፅ የሞገተው ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ባለፉት 9 ወራቶች በሰሜን አሜሪካ በሕክምና እና በፓርቲው ሥራ ላይ ከቆዩ በኋላ ግንቦት 23/2000 ዓ.ም አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡

 

      የኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ጤና ተሟልቶ ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ምክንያት በማድረግ በየደረጃው የሚገኙ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች አባላትና ታዋቂ የአገር ሽማግሌዎች በተገኙበት ቸርችል ጐዳና በሚገኘው የቅንጅት ጽ/ቤት ደማቅ አቀባበልና የሪሴፔሽን ግብዣ ተደርጐላቸዋል፡፡

      ኢንጅነር ኃይሉ በቅንጅት ጽ/ቤት ቅጥር ግቢ በተንጣለለ ድንኳን ውስጥ በብዛት ለተገኙት የትግል ጓደኞቻቸው ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ባስተላለፉት አጭር ቃል፣ ‹‹ጤንነቴ ተሟልቶ በምወዳት አገሬና ላይ ከማፈቅራቸው የትግል ጓደኞቼ መካከል በመገኘቴ በደስታ ተውጫለሁ ለዚህ ያበቃኝንም አምላኬን አመሰግናለሁ›› ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ፓርቲያችን ‹‹በዓለማ ፅናት በእውነትና በቁርጠኝነት ለሚመጡ ሁሉ በራችን ክፍት ነው፤ ነገር ግን ለሌላ አካል መልዕክተኛ ሆኖ መምጣት ግን ፈጽሞ የተከለከለ ነው፡፡ አገራችንን ለመገንባት ሕዝቡ ተፋቅሮ፣ ተከባብሮ፣ በእኩልነትና በአንድነት እንዲኖር ለማድረግ ሁላችንም የጋራ ኃላፊነት አለብን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእኛ ጋር ሲታገል ኖሮአል፤ የፓርቲ አባላት ያልሆኑ ወገኖቻችን እንኳን ለሕዝብ ዓላማ ሲሉ ተሰውተዋል፡፡›› ብለዋል፡፡

      በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ላይ አቶ አባይነህ ብርሃኑ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ የሥራ አስፈጻሚ አባል የእንኳን አደረሳችሁ ንግግር አድርገዋል፡፡ በንግግራቸውም ላይ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬ ከፓርቲያችን የሚጠብቀው በ1997 ዓ.ም በነበረው ምርጫ የታየውን የሰላምና የዴሞክራሲ ሻንፒዮን ሆነን እንደምንቀጥል ብቻ ነው›› ብለዋል፡፡

       የቅንጅት የአዲስ አበባ ሴቶች ተወካይ ወ/ሮ ዓለማየሁ ሞገድም የእንኳን ደህና መጡ ንግግር አድርገዋል፡፡ በንግግራቸውም ‹‹ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ ተዘግቶ የነበረውን ጽ/ቤት ከፍተው ሲሰሩ የነበሩ ቆራጥ ለእውነት የቆሙ የትግል አጋሮችዎ፣ ዋናው ጽ/ቤትን በመክፈት የቅንጅት ፓርቲን እንቅስቃሴ በአዲስ አበባና በመላው ኢትዮጵያ በማጠናከር የተዘጉ ቢሮዎች በመክፈት፣ የተበታተኑ አባላትን በማሰባሰብና ኰሚቴዎችን በማዋቀር ላደረጉት ታላቅ ሥራ በእርስዎ ፊት ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡›› በማለት ተናግረዋል፡፡

      እንዲሁም በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ወጣት ጌታነህ ዓለም የአዲስ አበባ ወጣቶችን በመወከል ባሰሙት ንግግር ወጣቱ ለኢትዮጵያ አንድነትና ለዴሞክራሲ መምጣት በኢንጅነር ኃይሉ ሻውል አመራር በቁርጠኝነት ለመታገል መወሰኑን አረጋግጠዋል፡፡ 

      በተጨማሪም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተወካይ ሻለቃ አርጋው ካብታሙ የኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ጤንነት ተሟልቶ ወደ አገር ቤት ተመልሰው በሕዝቡ መካከል በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ በመግለፅ ንግግር አድርገዋል፡፡ እንዲሁም የፓርላማ የቅንጅት አባላትን በመወከል የተከበሩ አቶ ሸዋፈራ ይጥና የእንኳን ደህና መጡ ንግግር አሰምተዋል፡፡

      ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ወደቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ጽ/ቤት እንደደረሱ ሁለት ሕፅናት እቅፍ አበባ ያበረከቱላቸው ሲሆን በሥነ ሥርዓቱ ላይ ከ300 በላይ የፓርቲው አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

      በዚሁ ሥነ ሥርዓት ላይ ታዋቂው የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞራሲ ፓርቲ የሞረሽ የኪነት ቡድን የተለያዩ ጣዕመ ዜማዎችን አሰምቷል፡፡

      ከቅንጅት ፓርቲ የወጣው ፕሮግራም እንደሚያስረዳው አቶ ኃይሉ ሻውል በዚሁ ሳምንት ለአገር ውስጥና ለዓለም ጋዜጠኞች ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡና በቀጣይ ጥቂት ቀናት ውስጥም ከቅንጅት ላዕላይ ምክር ቤት አባላት ጋር ሰፊ ውይይትና ምክክር ካደረጉ በኋላ የፓርቲያቸውን ጠቅላላ ጉባኤ እደሚጠሩ ታውቋል፡፡

      ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ባለፉት ወራቶች በመላ ኢትዮጵያ ባደረገው እንቅስቃሴ ከ20 በላይ የዞን ጽ/ቤቶች እንደተከፈቱና በሁሉም የኢትዮጵያ ወረዳዎች የሚንቀሳቅስ ኰሚቴዎች ማቋቋሙ ታውቋል፡፡  

      ስማችን፣ ዓርማችንና የምርጫ መወዳደሪያ ምልክታችን አላግባብ ለሌሎች ተሰጥቷል፣ ሲል ለመጀመሪያ ጊዜ የምርጫ ቦርድን በፍትሕ አደባባይ ያቆመው በኢንጅነር ኃይሉ ሻውል የሚመራው ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የክስ ሂደት መቀጠሉም ታውቋል፡፡

      ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ለሕክምና ሰሜን አሜሪካ በቆዩበት ጊዜ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን በማካሄድ የድጋፍ ሰጪ ቻፕተሮችን በማጠናከርና አዲስ ድጋፍ ሰጪ ቻፕሮተሮችንም በማቋቋም በአጠቃላይ ከእስር ከተፊቱ በኋላ በቅንጅት ከፍተኛ አመራሮች መካከል በተፈጠረው መካፋፈል ምክንያት፣ በውጭ አገር ደጋፊዎች መካከል የተነሱትን ጥያቄዎች በማብራራትና በማረጋጋት ከፍተኛ ሥራ ለፓርቲያቸው ሲሰሩ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡






Reddit!Del.icio.us!Facebook!Slashdot!Netscape!Technorati!StumbleUpon!Newsvine!Furl!Yahoo!Ma.gnolia!Free social bookmarking plugins and extensions for Joomla! websites! title=
Comments (0)Add Comment

Write comment
quote
bold
italicize
underline
strike
url
image
quote
quote
Smiley
Smiley
Smiley
Smiley
Smiley
Smiley
Smiley
Smiley
Smiley
Smiley
Smiley
Smiley

security code
Write the displayed characters


busy
 


Quick Jump

Ethio Date & Time

ዛሬ ቀኑ:

Calendar Converter




Daylight Saving