|
ተመራጩ የቅንጅት አባል ተገድለው ተገኙ
በሰሜን ሸዋ ዞን በሲደብርና ዋዩ ወረዳ በ1997 ዓ.ም በተካሄደው በተወካዮችና ክልል ምክር ቤት አባላት ምርጫ ለክልል ተወዳድረው ወያኔን በከፍተኛ ድምፅ ያሸነፋት አቶ ሙሉጌታ ተሾመ ሰኔ 1ዐ ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም በመጥረቢያ ተጨፍጭፈው ከተገደሉ በኋላ አስክሬናቸው ተጥሎ በነጋታው መገኘቱን የዓይን ምሥክሮች ገልፀዋል፡፡
ቀደም ሲል የአካባቢው ሹማምንት ሟቹን ተመራጭ ለማሰር ብዙ ጊዜ ሲያሳድዱት መቆየተቸውን ውስጥ አዋቂ ምንጮች አስረድተው በማያያዝም በአሟሟቱ ሁኔታ ላይ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ የአገዛዙ አካላት እጅ ሳይኖርበት እንዳልቀረ ጥርጣሬአቸውን አስቀምጠዋል፡፡
ሟች ሃያ ሰባ ዓመት ዕድሜ የነበራቸው ሲሆን አስክሬናቸውም በደነባ ቅድስ ጉዮርጊስ ቤተክርስቲያን መቀበሩን ምንጮች አክለው ተናግረዋል፡፡
በወቅቱ ምርጫው በመጭበርበሩ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ፓርላማ ላለመግባት ሲወስን አቶ ሙሉጌታ ውሣኔውን አክብረው ወደ ክልል ምክር ቤት ሳይገቡ መቅረታቸውን የመረጃ ምንጮች የገለፁ ሲሆን ገዳዮቹ እስካሁንም አለመያዛቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
አንድ የቅንጅት አባል ተገደሉ፡፡
በሰሜን ጎንደር በጭልጋ ወረዳ የኪቢናና የቻሊያ ደብር ገበሬ ማህበር የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ተጠሪ የነበሩት አቶ ለገሰ ተበጀ በቀበሌ የወያኔ አገልጋይ ታጣቂዎች በዱላ ክፉኛ ተደብድበው ሕክምና ቢደረግላቸውም ሊድኑ ባለመቻላቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ውስጥ አዋቂ ምንጮች ከጭልጋ ገልፀዋል፡፡
ሟቹ የቅንጅት አባል ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ከመመሥረቱ በፊት አንሥቶ ለኢትዮጵያ አንድነት፤ ለዴሞክራሲና ለሰላም በቡድንም ሆነ በተናጠል የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሲያደርጉ የኖሩ ጠንካራ ግለሰብ እንደነበሩ ምንጮቻችን አክለው ተናግረዋል፡፡
እንደ ውስጥ አዋቂ ምንጮች አገላለፅ ተጠርጣሪዎች ባሁኑ ወቅት ተይዘው የታሰሩ ቢሆንም የአካባቢው የወያኔ ሹማምንት ለማስፈታት ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ቀደም ሲል በደቡብ ጎንደር በፋርጣ ወረዳ በቁሃላ ገበሬ ማህበር ውስጥ ምሥጋናው ጌጤ ዘለለው የተባለ የአሥራ ዘጠኝ ዓመት ወጣት በወያኔ ቅጥረኛ ፖሊሶችና በአካባቢው ታጣቂዎች ክፉኛ ተደብድቦ መገደሉ ይታወሣል፡፡
እንዲሁም ከተማ መሸሻ የተባለ ሰላሣ ዓመት ዕድሜ የነበረው የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አባል በደቡብ ወሎ በደሴ ከተማ ውስጥ ባልታወቁ ሰዎች ተደብድቦ ሲሰቃይ ቆይቶ መሞቱን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡
|