|
ሕዝቡ ከሱዳን ጦር ጋር እየተዋጋ መሆኑ ተገለጠ |
|
|
|
Monday, 07 July 2008 |
|
በሰሜን ጎንደር ዞን በቋራና በሑመራ ወረዳዎች ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቆ ከገባው ከሱዳን ጦር ጋር ሕዝቡ በመዋጋት ላይ እንደሚገኝ ሰሞኑን ጦርነቱን ሸሽተው የመጡ የዓይን ምስክሮች ገለጡ፡፡
የወያኔን ሥርዓተ አገዛዝ መከታ አድርጎ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቆ የገባው ይህ የሱዳን ጦር በሕዝቡ ንብረት ላይ ከፍተኛ ዘረፋ ያካሄደ ሲሆን ከወገን በኩል የሞቱና የቆሰሉ መኖራቸውንም የዓይን ምሥክሮች አረጋግጠዋል፡፡
እንደ ዓይን ምሥክሮች አገላለፅ ጦርነቱ ከዛሬ 12 ቀን በፊት ተቀስቅሶ አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ የቀጠለ ሲሆን በወረዳዎቹ ውስጥ የሚገኙ የኢትዮጵያ የሥርዓተ- አገዛዙ ጦር አባላት ግን ከማንም ሳይወግኑ በገለልተኝነት መቆማቸው ተመልክቷል፡፡
ባአሁኑ ወቅት የሁለቱን ሀገሮች ድንበር እንደገና ማካለል በሚል ሰበብ የወያኔ አገዛዝ መሬት ከኢትዮጵያ ቆርሶ ለሱዳን ሊሰጥ ማቀዱን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በከፍተኛ ሁኔታ በመቃወም ላይ ሲገኝ በውስን ደረጃ የሥርዓተ- አገዛዙ ታጣቂዎችም በግልፅ ተቃውሞ እያቀረቡ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚሁ በሰሜን ጎንደር ዞን በዳባት ደጋማው ክፍል ካድሬዎች እንዲሁም የሥርዓተ - አገዛዙ አካላት ስለሱዳንና ኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያትተውን ሰነድ አዘጋጅተው ከላይ የተጻፈውን ዝርዝር ደብቀው በመያዝ አርሶ አደሮችን እያስገደዱ በማስፈረም ላይ መሆናቸውን የዐይን ምሥክሮች ከቦታው ገለጡ፡፡
አንዳንድ ውስጥ ዐዋቂዎች ይህ ሰነድ አርሶ አደሮች መሬቱ ለሱዳን ተቆርሶ እንዲሰጥ የተስማሙ ለማስመሰል የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
|