RSS 2.0 Email us: webmaster@mahder.com

Ethiopia: Mahder.com -Ultimate Ethiopian News and Information Portal

Thursday
Aug 21st
Home arrow News arrow የቅንጅት የውጭ ድጋፍ መልዕክቶች ሲዳሰሱ - ከታዴዎስ ታንቱ
የቅንጅት የውጭ ድጋፍ መልዕክቶች ሲዳሰሱ - ከታዴዎስ ታንቱ Print E-mail
Monday, 07 July 2008

ከታዴዎስ ታንቱ

     ሕዝባዊ መሠረት ያለው የፖለቲካ ፓርቲ በፍጻሜው የድል ነዶ ያስራል፡፡ የእኩያን ዓላማም እንደ ጤዛ ተንኖ እንደ ጉም ይበንናል፡፡ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲም ህዝባዊ ድል ለመጎናፀፍ በመገስገስ ላይ ይገኛል፡፡ የሰሞኑ 1ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ለዚህ በቂ ማስረጃ ሊሆን በቅቷል፡፡

     ጉባኤተኞቹ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡ ናቸው፡፡ የጉባኤው አባላት ከሰሜን ሸዋ፣ ከምሥራቅ ሸዋ፣ ከደቡብ ወሎ፣ ከሰሜን ወሎ፣ ከሰሜን ጎንደር፣ ከደቡብ ጎንደር፣ ከምሥራቅ ጎጃም፣ ከምዕራብ ጎጃም፣ ከደቡብ ሸዋ፣ ከጌዴኦ፣ ከከፋ፣ ከቦረና፣ ከጉጂ፣ ከሸካ፣ ከባሌ፣ ከጅማ፣ ከጋሞ፣ ከወላይታ፣ ከጎፋ፣ ከዳውሮ፣ ከአዋሳ፣ ከሲዳማ፣ ከትግራይ፣ ከድሬዳዋ፣ ከምዕራብ ሐረር፣ ከምሥራቅ ሐረር፣ ከሶማሌ፣ ከአፋር፣ ከአርሲ፣ ከአዲስ አበባና ከሌሎችም ክፍላተ አገር መጥተው በዚህ ታሪካዊ ጉባዔ ላይ ንቁ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ የተለያዩ ውሳኔዎችንም በዓላማ ፅናትና በቁርጠኝነት ያሳለፋ ከመሆኑም በላይ ለተግባራዊነታቸው የአሠራር ስልቶችን ቀይሰዋል፡፡ በጉባዔው ውጤት የኢትዮጵያ ሕዝብ ረክቷል፡፡ በመሆኑም ሕዝቡ ከቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ጋር ተሰልፏል፡፡

     ይህን ሐቅ ከቶም ማስተባበል የማይችሉ አንጀኞችና መሰሎቻቸው ከኢትዮጵያ ውጭ የሚገኙ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች ከቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ እየራቁ የሄዱ አስመስለው ያወራሉ፡፡ ይልቁንም ድጋፍ ሰጪዎች ከእነሱ ጋር እንደወገኑ አድርገው አሉባልታ ይነዛሉ፡፡ አንዳንድ ጋዜጣ ተብዬዎችም ፅፈውላቸዋል፡፡ እውነታው ግን በተቃራኒ መስመር ላይ ተቀምጧል፡፡ ሐሰት አይደለም፡፡ ሐቅ ነው! በውጭ አገሮች የሚገኙ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች ከቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ጋር በቁርጠኝነት ቆመዋል፡፡ ይህን ደግሞ በተግባር አስመስክረዋል፡፡ በጉባዔው ሂደት ስኬታማነቱን በመመኘት መልዕክቶችን ልከዋል፡፡ መልዕክቶቻቸውም ለጉባዔው በንባብ ተሰምተዋል፡፡ በመጠኑ እስቲ እንዳስሳቸው!

     በቅድሚያ ወደ ቅንጅት ዓለም አቀፍ የአማካሪዎች ቦርድ እናምራ! ከዶክተር ታዬ ጋር አንድ አፍታ! ዶክተር ታዬ ወልደሰማያት የቅንጅት ዓለም አቀፍ አማካሪዎች ቦርድ ሊቀመንበር ናቸው፡፡ ዶ/ር ታዬ ክቡር ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ችግሮች ለመፍታት እና በወህኒ ቤት በነበሩበት ወቅት ያደረባቸውን ሕመም ለመታከም ወደ አሜሪካ ሄደው በሕክምና ላይ በነበሩበት ወቅት ለኢትዮጵያ ታላቅ ድጋፍ ይሆናል ያሉትን የቅንጅት ዓለም አቀፍ የአማካሪዎች ቦርድን ማቋቋማቸውን አስታውሰው "ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል በሕመማቸው ምክንያት ዓላማቸው ሳይዛባ፤ ግባቸው ሳይጣመም በህመም ላይ ቢሆኑም እንኳ አገሬን አልተውም በማለት ወደ አገራቸው በመመለሳቸውና ይህን ጉባዔ እውን እንዲሆን በማድረጋቸው የማይዛባ ሕሊናቸውንና ያገር ፍቅራቸውን በዚህ አጋጣሚ እናደንቃለን፡፡ የዛሬው ጉባዔ በሚያጸድቀው ውሳኔ በመታገዝ ከፓርቲያችንና መሪያችን ጋር በመተሳሰብና በመረዳዳት በቅን መንፈስ ለመስራትና አገራችንን ከወደቀችበት ለማንሳት በሚደረገው ማንኛውም ሰላማዊ ትግል የማንለያችሁ መሆኑን እያረጋገጥን እውነትንና ሕዝቡን ይዛችሁ ከታቀደበት የዕድገትና የነጻነት ቀን እንደምንደርስ አንጠራጠርም፡፡" ብለዋል፡፡

     "ይህ ጉባዔ ይጠበቅ የነበረ ሲሆን ተካሂዶ ለውጤት መብቃቱ ያስደስታል" ያሉት ደግሞ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ የሜንሶታ ቻፕተር ሊቀመንበር ሲሆኑ በመቀጠልም ከትግል አጋሮቻቸው ጋር በመሰለፍ በቅንጅት ስም በትጋት ሰርተው ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

     አቶ ግዛው ተስፋዬ በሰሜን አሜሪካ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ድጋፍ ሰጪ ማኀበር ሊቀመንበር ናቸው፡፡ በጉባዔው ሂደትም መልዕክት ልከዋል፡፡ በመልዕክታቸውም "እኛ በውጭ አገር የምንገኝ ወገኖቻችሁ በአገራችን ላይ የሚካሄደውን ደባና ተንኮል ለመታገል በቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ሥር መሰባሰባችን ይታወሳል፡፡ ቅንጅት በኢትዮጵያ የትግል ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የያዘና በዓለም ጉድ የተባለውን የምርጫ 97 ታሪክ የሰራ ድርጅት ቢሆንም በከፋፋዮች በተቃጣበት አደጋ ከአገር ቤት አልፎ በዚህ በዲያስፖራውም ላይ ትልቅ ችግር ተከስቶ ነበር፡፡ ሆኖም በኢንጅነር ኃይሉ ሻውል መሪነት በተካሄደው ጉብኝት እውነቱ እየጠራ በመምጣቱ ማን የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጅ መሆኑ የተለየበት ወቅት ላይ ደርሰናል፡፡" ካሉ በኋላ በመቀጠልም "በተለይም ከዚያ ውጣ ውረድ በኋላ የሚካሄደው ይህ የጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ የኢትዮጵያንና የሕዝቧን ዕጣ ፈንታ ለመወሰን የጠራ በመሆኑ በመላው ዓለም የሚገኙ ተወላጆች በጉጉት ይጠብቁታል፡፡ እኛ በየቻፕተሩ ተደራጁተን የምንገኝ ወገኖቻችሁ ኢንጅነር ኃይሉ ሻውልና ፓርቲያችን በሚሰጡን መመሪያ መሠረት በሰላማዊ ትግሉ ውስጥ በሁለንተናችን እንደምንሳተፍ ስናረጋግጥ በታላቅ ደስታ ነው" ብለዋል፡፡ አቶ ግዛው በመልዕክታቸው መደምደሚያ ላይ "ኢትዮጵያ አንድ ናት! እኛም አንድ ነን!" በማለት የኢትዮጵያ አንድነት እንደማይገሰስ አረጋግጠዋል፡፡

     አቶ ዘነበ ዓለማየሁ በሰሜን አሜሪካ የዲሲ ቻፕተርና የሥነ ምግባር ኰሚቴ ሊቀመንበር ናቸው፡፡ የዓላማ ፅናታቸውንና ቁርጠኝነታቸውን የሚያረጋግጥ መልዕክት በኰሚቴው ስም በጉባዔው ሂደት ለጉባዔው አስተላልፈዋል፡፡ በጥቂቱ ቀንጭበናል፡፡ "ካልቆረጡ ከግቡ አይደረስምና በመቁረጣችሁ ከዚህ ደርሳችኋል፡፡ ውድ የጉባዔው አባላት ጉባዔው በወጣለት ፕሮግራም መሠረት ተፈላጊውን ተግባር አከናውኖ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ልዕልና፤ ሰላም፤ አንድነት፤ ነፃነት ዕኩልነትና ዴሞክራሲ እውን መሆን የሚያስችል የትግል ስልትና ግብ ቀምሮ እንደሚነሳ እምነታችን የፀና ነው፡፡ እኛም የጉባዔውን ውሳኔዎች ተግባራዊ ለማድረግ ከመሪያችን ኢንጅነር ኃይሉ ሻውል ጋር በቁርጠኝነት በተጠንቀቅ ላይ ያለን መሆናችንን ስንገልፅ በታላቅ አክብሮት ነው፡፡"

     አቶ ቢሹ ማሞ በካናዳ የቅንጅት ድጋፍ ጽሕፈት ቤት ሊቀመንበር በበኩላቸው ከቶሮንቶ ካናዳ በጽሕፈት ቤቱ ስም ለጉባዔው ባስተላለፉት መልዕክት "የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጣለበትን እምነትና ተስፋ አደራና ኃላፊነት ተሸክሞ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ፣ መሪዎቹ፣ አባላቱና ደጋፊዎቹ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለው ይኸው ዛሬ የመጀመሪያውን ጉባዔ ለማካሄድ በመብቃቱ በእውነቱ ለኢትዮጵያ ዳግም ትንሳዔ ነው ማለት ይቻላል፡፡" ካሉ በኋላ በመቀጠልም "በካናዳ የቅንጅት የባህልና የእርዳታ ድርጅት በቶሮንቶ በመባል የሚታወቀው የቅንጅት ድጋፍ አካል ከድሮም ጀምሮ በጠንካራ አባላቱ ድጋፍ እስከአሁን ቆይቷል፡፡ ለማፈራረስ የተሞከረው ሙከራ ሁሉ ከሽፎ ጽሕፈት ቤቱ ሳይዘጋ የቦርድ አባላቱ ሳይከፋፈሉ በአንድነቱ ጸንቶ የቆየ ድጋፍ ሰጭ ድርጅት ነው፡፡

     የቅንጅትን ስምና አርማ ለማስከበርና ለመጠበቅ ባረግነው ጥረት የቶሮንቶ የቅንጅት ድጋፍ ጽሕፈት ቤት በካናዳ በፌዴራል መንግሥት ደረጃ ሕጋዊ ባለቤት ሆነን አስከብረናል፡፡  የቅንጅት ስሙንና አርማውን ያለአግባብ የተጠቀሙበትን ተለጣፊዎች በሕግ ፊት አቅርቦ በሂደት ላይ ይገኛል፡፡ ዛሬ ማንም ተለጣፊም ሆነ ሰርጎ ገብ የቅንጅትን ስምና አርማ ሊጠቀምበት አይችልም፡፡ በአገር ቤትም ስምና አርማውን ለማስከበር በሕግ የያዛችሁትን ትግል ቀጥላችሁ እንደምታስከብሩ ተስፋ እናደርጋን፡፡" ብለዋል፡፡

     በተጨማሪም ዶክተር አበበች በላይ በብሪታኒያ የቅንጅት ድጋፍ አመራር ኮሚቴ ሊቀመንበር ለጉባዔው ባስተላለፋት መልዕክት "ምንም እንኳን ጉዞው ውጣ ውረድ የበዛበትና ከባድ ቢሆንም ቅንጅት የተከተለው የሰላም ትግል ትክክል መሆኑ ዛሬ በሚታየው ተጨባጭ ሁኔታ ሊረጋገጥ ችሏል" ካሉ በኋላ አያይዘውም "ቅንጅት በፀዳ የሞራልና የህሊና ፍልስፍና ላይ የቆመ ስለሆነ በሀገር አንድነትና በሕዝብ መብት ክብር ቁማር ለመጫወት ፈቃደኛ አለመሆኑን አጋግጧል፡፡" ብለዋል፡፡

     እንዲሁም አቶ አምሃ ውበቱ በሰሜን አሜሪካ የቅንጅት ማኀበር የተኒሲ የቦርድ ሊቀመንበር፤ አቶ ሰሎሞን ተፈራ በሰሜን አሜሪካ ቅንጅት ማኀበር የናሸቪል ተነሲ ቻፕተር ሊቀመንበር፤ ወ/ሮ የኔዓለም ከበደ በሰሜን አሜሪካ የቅንጅት ድጋፍ ሰጪ ማኀበር የዴንቨር ቻፕተር ሊቀንበር፤ አቶ ይልማ አክሊሉ በሰሜን አሜሪካ የማንፌስ ተነሲ የቅንጅት ድጋፍ ሰጪ ቻፕተር ሊቀመንበር አቶ አበበ ክብረት በዳላስና ፎርትዎርዝ ቴክሳስ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ መልዐኩ ተፈራ በሰሜን አሜሪካ የቨርጅኒያ የቅንጅት ድጋፍ ሰጪ ቻፕተር ሊቀመንበርና የቦርድ አባል፤ አቶ አማረ ፋንቱ በሰሜን አማሪካ የቅንጅት ድጋፍ ሰጪ ማኀበር የሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ ቻፕተር ሊቀመንበር፣ የሳንዲአጎ የቅንጅት ድጋፍ አካልና አቶ መልአኩ በየነ ከኡጋንዳ፤ ጉባዔው እየተካሄደ ሳለ ለጉባዔው ያላቸውን አክብሮትና አድናቆት በመግለፅ መልዕክቶቻቸውን አሰምተዋል፡፡ በተጨማሪም አቶ ጌታቸው ዋና፤ አቶ ደመረ ኃ/ማርያምና አቶ ኢዛና ደገፉ ከአውሮፓ በስልክ ለጉባዔው መልዕክት ልከዋል፡፡ የቅንጅት ድጋፍ ሰጪና የልማት ማኀበር በበኩሉ ለጉባዔው የድጋፍ መልዕክት አስተላልፏል፡፡ በተጨማሪም አቶ ጌታቸው አሰፋ በሰሜን አሜሪካ የቅንጅት ድጋፍ ሰጪ ማኀበር የኣሀዮ ቻፕተር ሊቀመንበር፤ አቶ ኤርምያስ ከበደ በሰሜን አሜሪካ የካሊፎርኒያ ግዛት የፍሬዝኖ የቅንጅት ድጋፍ ማኀበር ሊቀመንበርና የቦርድ አባል፤ አቶ ካሣ አማረ በሜሪካ የቅንጅት ድጋፍ ሰጪ ማኀበር የሳክራሜንቶ ቻፕተር ሊቀመንበር፣ አቶ አበበ ክብረት በሰሜን አማሪካ የዳላስ ድጋፍ ሰጪ ማህበር ሊቀመንበርና ሌሎችም ለቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ጉባዔ የድጋፍ መልዕክት በቁርጠኝነት አቋም አስተላልፈዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የሰሜን አሜሪካ የቅንጅት ድጋፍ ማህበር የቀድሞ አመራር አባላት ሻለቃ ዮሴፍ ያዘው፤ ዶክተር ስዩም ሰሎሞን፤ ዶክተር ጋሹ ሀብቴ፤ አቶ ተስፋዬ መንግሥቱና ኢንጅነር ሞገስ ብሩክ ለፓርቲው እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሕዝብ መልካሙን ሁሉ በመመኘት ለጉባዔው መልዕክት ልከዋል፡፡  ከሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በአንድነት መቆማቸውን ዳግም አረግጠዋል፡፡

     ስለዚህ በውጭ አገር የሚገኙ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች ሁሉ ከቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ጎን መሆናቸውን ወዳጅም ሆነ ጠላት ባግባቡ ይረዳ፡፡ ቅንጅት አንድ ነው! አሳሳቾች ግን ብዙ ናቸው፡፡ ትክክለኛ ግንዛቤና እውቀት ሊኖረን ይገባል፡፡ ተሳስተው ሌላውን የሚያሳስቱ ይታረሙ! ቅንጅት መስከረም 14 ቀን 1998 ዓ.ም የተዋሃደው ነው! ሕዝብ ከቅንጅት ጋር ነው! ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች ከቅንጅት ጋር ናቸው! ስለዚህ አንጀኞች፤ከፋፋዮችና አሉባልተኞች እርማቸውን ያውጡ! እንላለን!






Reddit!Del.icio.us!Facebook!Slashdot!Netscape!Technorati!StumbleUpon!Newsvine!Furl!Yahoo!Ma.gnolia!Free social bookmarking plugins and extensions for Joomla! websites! title=
Comments (0)Add Comment

Write comment
quote
bold
italicize
underline
strike
url
image
quote
quote
Smiley
Smiley
Smiley
Smiley
Smiley
Smiley
Smiley
Smiley
Smiley
Smiley
Smiley
Smiley

security code
Write the displayed characters


busy
 


Other top stories


Quick Jump

Ethio Date & Time

ዛሬ ቀኑ:

Calendar Converter




Daylight Saving