|
ጌታነህ ዓለም
ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ በኢትዮጵያ ምድር ሰፊ ሕዛባዊ መሠረት ያለው ብቻ ሳይሆን በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትየጵያውያን ወገኖቻችንም ጭምር ከፍተኛ ድጋፍ የሠጡት መሆኑ ይታወቃል፡፡ እንዲሁም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰላም ወዳዶችና ዴሞክራትክ ኃይሎች ሁሉ ለዚህ ፓርቲ ያላሰለሰ ድጋፍ ሰጥተዋል፡፡ ለዚህም በግንቦት ወር 1997 ዓ.ም የተካሄደው የተወካዮችና የክልል ምክር ቤቶች የምርጫ ውጤት በተጭበረበረበት ወቅት ከአራቱም ማዕዘናት የተሰማው የቁጭትና የተቃውሞ ድምጽ በራሱ በቂ ማስረጃ ነው፡፡
በገዥዎች ትዕዛዝ ከግለሰቦች የድጋፍ ፊርማ ለቅሞ ሕልውናውን ያወጀ አስመሳይ ሳይሆን ከፅኑ ሕዝባዊ መሠረት ላይ ተነስቶ ሥጋና ደም ለብሶ መስከረም 14 ቀን 1998 ዓ.ም ከሕዝብ ማህፀን የተወለደው ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ከሰኔ 14 ቀን 2000 ዓ.ም አንስቶ ለሁለት ተከታታይ ቀናት 1ኛ መደበኛ ጠቅለላ ጉባዔ ማካሄዱ ይታወሳል፡፡ በዚህ ጉባዔ ላይ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡ ጉባዔተኛ የተሳተፉ ሲሆን የአቋም መግለጫም አውጥተዋል፡፡ በጉባዔው ላይ የፓርቲው የሴቶችና የወጣቶች ክንፍ አመራር አባላትም በንቁ ተሳትፎ ተገኝተዋል፡፡ እኛም በጉባዔው ላይ ከተገኙት የወጣት አመራር አባላት መካከል ለዛሬው አንዱን አነጋግረናል፡፡ ወጣት ጌታነህ ዓለም ይባለል፡፡ ጌታነህ ዓለም በፓርቲው በወጣቶች ክንፍ የአዲስ አበባ ወጣቶች አስተባባሪ ነው፡፡ "በሀገራችን አዲስ የፖለቲካ ባህል ለማምጣት ወጣቱ ምን ያህል ዝግጁ ነው?" የሚል ጥያቄ ቀዳሚው ነበር፡፡ መልስ አለው፡፡ እነሆ!
"ወጣቱ እንደ ትላንቱ ሁሉ ዛሬም የሀገሩን ሁኔታ በንቃት በመከታተል ላይ ይገኛል፡፡ የዚህች ሀገር ችግር ደግሞ በሰላማዊ መንገድ መፈታት እንዳለበት አጥብቆ ያምናል፡፡ ለሰላማዊ ሽግግር ይታገላል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ራሱ መሾምና መሻር እንዳለበት በቂ ግንዛቤ ጨብጧል፡፡ የሕዝቡን ችግር ለዘለቄታው ለመፍታት ሳያሰልስ ያስባል፡፡ ወጣቱ በሰላማዊ ትግል የኢትዮጵያን ትንሳኤ ማየት ይፈልጋል፡፡ ሀገራችን ሌሎች ከደረሱበት የዕድገትና የብልፅግና እርከን እንድትደርስ የበኩሉን አስተዋጽኦ ሁሉ ለማድረግ በፅኑ የኃላፊነት አቋም ይንቀሳቀሳል፡፡ ሰላማዊ ትግሉ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያምናል፡፡
"እርግጥ ነው፡፡ ወጣቱ ችግሮች አሉበት፡፡ የሥራ እጥነት ችግር ከፍተኛ ደረጃ ደርሷል፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ በኑሮ ውድነት በመሰቃየት ላይ ይገኛል፡፡ የኑሮ ሁኔታ ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ ይሄዳል፡፡ ምንም መሻሻል አይታይበትም፡፡ በዚህ ላይ ሥራ አጥነት ሲታከልበት የኑሮ ጫና መቋቋም ከሚቻለው በላይ እየሆነ መጥቷል፡፡ በጣም ከብዷል፡፡ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ይህን ችግር ግን መዋጋት አለብን፡፡ ወጣቱ ችግሮቹን ሁሉ በስልትና በብልሀት ይዋጋ፡፡ እየተዋጋም ነው፡፡ ሌላ አማራጭና አቋራጭ መንገድ ፈጽሞ የለም፡፡ ትግል ነው መፍትሄው! ወጣቱ ባሁኑ ወቅት በመሪ ድርጅቱ በቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ዙሪያ እየተሰባሰበ ነው፡፡ አቋሙን ይበልጥ አጠናክሮ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተባብሮ ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮቹን ይፈታል፡፡ በሀገራችን አዲስ የፖለቲካ ባህል ለማምጣትም በቂ የሥነ ልቦና ዝግጅት አድርጎ ሰላማዊ ትግሉን በቁርጠኝነት ተያይዞታል፡፡"
በመቀጠልም " ወጣቱ በቅርቡ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ጉባዔ አቋም መግለጫው ያሳላፋቸውን ውሳኔዎች ተግባራዊ ለማድረግ ምን ያህል ተዘጋጅቷል፡፡" ተብሎ ተጠይቋል፡፡ ጌታነህ ዓለም ለዚህ ጥያቄም መልስ ሰጥቷል፡፡ እንዲህ በማለት፡፡
"የፓርቲችን ወጣቶች በተዋረድ ማዕከላዊነትን ጠብቆ የሚመጣ ትዕዛዝ ሁሉ ተግባራዊ ለማድረግ ተዘጋጅተናል፡፡ ይህ ፅኑ አቋማችን ነው፡፡ ፈፅሞ አናቅማማም፡፡ ስለዚህ ከሴቶች፣ ከምሁራንና ከጎልማሶች ጋር ተባብረን በአቋም መግለጫው የተመለከቱትን ውሳኔዎች ተግባራዊ እናደርጋለን፡፡ ፓርቲው የሚያወጣቸው መመሪያዎች ሁሉ ተፈጻሚ ለማድረግ በቂ ዝግጅት አድርገናል፡፡ ለዋሣኔዎቹ ተግባራዊነት ተነሥተናል፡፡ በቁርጠኝነት በመንቀሳቀስ የውሳኔዎችን ተፈፃሚነት ለማረጋገጥ እኛ ወጣቶች ከምን ጊዜውም በበለጠ ዝግጁ መሆናችን ሊታወቅ ይገባል፡፡
"ወጣቱ ከራሱ በሰረጹ ድክመቶች በልዩ ልዩ ሱሶች ስለመጠመዱ ምን አስተያት አለህ?" ተብሎ ለተጠየቀው ደግሞ ወጣት ጌታነህ ሲመልስ እንዲህ ብሏል፡፡
"እርግጥ ነው! ወጣቱ ከራሱ ከግሉ በሠረጹ ድክመቶች ሲጎዳ ይስተዋላል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ወጣቶች በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች አሉ፡፡ በከተሞች ብቻ ሳይሆን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖራቸውንም አንዘንጋ፡፡ በልዩ ልዩ ሱሶች አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የሚጠመዱ ወጣቶች ከብዙሃኑ ወጣት ጋር ሲነጻፀር ግን በቁጥር ብዙ አይደሉም፡፡ አብዛኛው የኢትዮጵያ ወጣት ብቁና ንቁ ነው፡፡ ያገሩን ሁኔታ በጥንቃቄ ይከታተላል፡፡ ሀገራችን በዚህ በተዋረደ ሁኔታ ላይ መገኘቷ ያስጨንቀዋል፡፡ ይቆጨዋልም፡፡ ለኢትዮጵያ ዳግሞ ትንሳኤ በሰላም ሐዋርያነት የሚጠበቅበትን ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ መሆኑም በተግባር ታይቷል፡፡ በዚህም እኛ ወጣቶች ኩራት ተሰምቶናል፡፡
"አንድ መዘለል የሌለበት ጉዳይ ግን አለ፡፡ ወጣቱ ለምን ሥራ አጥ ሆነ? ለምን በሱሶች ተጠምዶ ራሱን ይጥላል?" የሚሉትንና ተዛማጅ ጥያቄዎችን እስቲ በቅድሚያ እናንሳ፡፡ ተገቢ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል፡፡ የወጣቱ ችግር ከሥርዓቱ ባሕርይ ይመነጫል፡፡ መልካም አስተዳደር የለም፡፡ ሥረዓተ-አገዛዝ ለወጣቱ ሁለንተናዊ ችግር በቀጥታ ተጠያቂ ነው፡፡ አንዳንድ ተጨባጭ ሁኔታዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሁላችንም በውል እናውቃለን፡፡ እንደ ድሮው በመላው ኢትዮጵያ እንደ ልብ ተዘዋውሮ ሥራ መሥራት አስቸጋሪ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ማንም ይህን ያውቀዋል፡፡ ዛሬ እንደ ልብ ለመንቀሳቀስ መንገድ ዝግ ነው፡፡ በተለይ የክልል አስተዳደሮች ሁኔታዎችን በጣም አጥብበውታል፡፡ የዘረኝነት ድርጊቶችም በአንዳንድ አካባቢዎች ተስተውለዋል፡፡ ይህ ሁኔታ እንግዲህ የወጣቱን ተንቀሳቅሶ የመሥራት መብት ይጻረራል፡፡ የወጣቱን ውስን ችግሮች እንዲባባሱ ያደርጋል፡፡ ወጣቱ ተስፋ ወደ መቁረጥ እንዲያዘነብል ይገፋፋዋል፡፡ ተስፋ የቆረጠ ወጣት ደግሞ ሀገር ሊረከብ አይችልም፡፡ ሱሰኛ ወጣት ለኃላፊነት አይበቃም፡፡ ይህ ችግር ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡ ችግሩ ሊቀረፍ የሚችለው መልካም አስተዳደር ሲዘረጋ ነው፡፡ ወጣቱ አቅሙና እውቀቱ እስከፈቀደ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ተዘዋውሮ መሥራትና መኖር መቻል አለበት፡፡ ለኢትዮጵያ ወጣቶች መሰናክል የሆኑትን ሥርዓቱ ያመጣቸውን ፈርጀ-ብዙ ችግሮች ሁሉ ለማስወገድ ወጣቱ እውቀቱንና ጉልበቱን አስተባብሮ ሰላማዊ ትግሉን በሰላማዊ አካሔድ ማፋፋም አለበት እላለሁ፡፡"
|