|
በጌዴኦ ዞን አንድ የቅንጅት አባል ተገደለ |
|
|
|
Sunday, 20 July 2008 |
|
በደቡብ ኢትዮጵያ በጌዴኦ ዞን በወናጎ ወረዳ በዓለም ሆቴል ቤት ውስጥ በአስተናጋጅነት ተቀጥሮ ይሠራ የነበረ አስቻለው ባዬ የተባለ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አባል በአንድ የወያኔ ፖሊስ አባል በተተኮሰ ጥይት ሐምሌ 2 ቀን 2000 ዓ.ም ተገደለ፡፡
22 ዓመት ዕድሜ የነበረው ይህ ወጣት መገደሉን በመቃወም በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጉንም የዐይን ምስክሮች ከስፍራው ገልፀዋል፡፡
በዚሁ ሕዝቡ ከወናጎ ተነስቶ እስከ ዲላ ድረስ ባካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ "ቅንጅትን መምረጥ ወንጀል አይደለም! እኛ ራሳችንን እናስተዳድራለን! ውጡልን!" የሚሉትና ተዛማጅ መፈክሮች የተያዙ ሲሆን ሰልፈኞቹ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ድረስ ዘልቀው ተቃውሞአቸውን ማሰማታቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
የወጣት ሀብታሙ ባዬ የቀብር ሥነ-ሥርዓት በወናጎ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ቁጥሩ የበዛ ሕዝብ በተገኘበት ሐምሌ 3 ቀን 2000 ዓ.ም ተፈፅሟል፡፡
በተመሳሳይ ዜናም በደቡብ ኢትዮጵያ በጌዴኦ ዞን በወናጎ ወረዳ በወናጎ ከተማ ከአንድ ወር በፊት መሐመድ በተባለው የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፖርቲ ደጋፊ ላይ ሽጉጥ ተኩሶ አንድ እግሩን በጥይት የሰበረው ባሻ ተረፈ ኡዴ የተባለ የሥርዓተ-አገዛዙ አገልጋይ በሕዝቡ አስገዳጅነት ሐምሌ 3 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም ተይዞ መታሰሩን ከወናጎ የደረሱን የመረጃ ምንጮች አመለከቱ፡፡
ባሻ ተረፈን አስገድዶ በመያዝ እንዲታሰር ለፖሊስ ያስረከበው በወናጎ ከተማ ውስጥ አስቻለው ባዬ የተባለው የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አባል ሐምሌ 2 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም በአንድ የፖሊስ ባልደረባ መገደሉን በመቃወም ለሰላማዊ ሰልፍ የወጣው ሕዝብ መሆኑን ምንጮች ከወናጎ ገልፀዋል፡፡
ታሣሪው ባሻ ተረፈ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከእሥር ቤት እንዳይለቀቅ ህብረተሰቡ ራሱ ክትትል በማድረግ ላይ መሆኑንም ምንጮች አክለው አስረድተዋል፡፡
እግሩን በጥይት የተሰበረው ወጣት መሐመድ የአንድ ልጅ አባት ሲሆን ባሁኑ ወቅት የአልጋ ቁራኛ ሆኖ መቅረቱንም የመረጃ ምንጮች ገልፀዋል፡፡
|