|
አንድ የቅንጅት ደጋፊን የገደለው እጁን ሰጠ |
|
|
|
Thursday, 24 July 2008 |
|
በደቡብ ኢትዮጵያ በጌዴኦ ዞን በዲላ ዙሪያ ወረዳ በዋላሜ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ቱሬ ዲኦ የተባሉትን የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ደጋፊን ሐምሌ 5 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም በጥይት ገድሎ የተሰወረው ለማ የተባለ የሥርዓተ አገዛዙ የቀበሌ ታጣቂ ከሕግ ሊያመልጥ እንደማይችል አውቆ ሰሞኑን በሲዳማ ዞን ለጭኮ ወረዳ ፖሊስ እጁን ሰጠ፡፡
በሥልጣን ላይ ላለው አገዛዝ የማምለክን ያህል ፍቅር የነበረው ይህ ነፍሰ ገዳይ ወንጀሉን ፈፅሞ እስከ ተሰወረበት ዕለት ድረስ በዲላ ዙሪያ ወረዳ በዋላሜ ቀበሌ ማህበር ውስጥ የጦር መሣሪያ ታጥቆ ንፁሐን ዜጎችን ሲያፈራራ የኖረ መሆኑ ታውቋል፡፡
ግለሰቡ ቱሬ ዲኦን በጦር መሣሪያ መግደሉ እንደተሰማ የዲላና የአካባቢው ሕዝብ በቁጣ ገንፍሎ ወደ መኖሪያ ቤቱ በማምራት ቤቱን አፈራርሶ እንዳልነበረ ማድረጉንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
የቱሬ ዲኦ የቀብር ሥነ ሥርዓት በጌዴኦ ዞን በአባያ ወረዳ በሜኤሣ ቀበሌ ውስጥ ሐምሌ 6 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም መፈፀሙ ታውቋል፡፡
አንዳንድ የዲላ ከተማ ነዋሪዎች በጌዴኦ ዞን ውስጥ ንፁሐን ዜጎች በየወቅቱ በአገዛዙ ቅጥረኛ አገልጋዮች መገደላቸው ክፉኛ ያስቆጣቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል በዚሁ ዞን በወናጎ ወረዳ በወናጎ ከተማ አስቻለው ባዬ የተባለ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አባል ባንድ ቅጥረኛ ፖሊስ ሲገደል እንዲሁም መሐመድ የተባለ የቅንጅት ፓርቲ ደጋሬ በዚሁ በወናጎ ከተማ ባሻ ተረፈ ኡዴ በተባለ ፖሊስ በተተኰሰ ጥይት እግሩን መሰበሩ ይታወሳል፡፡
|