|
የቅንጅት አባላት በፍርድ ቤት ቀጠሮ መጉላላታቸውን ገለጡ |
|
|
|
Friday, 25 July 2008 |
|
ለሶስተኛ ጊዜ በተካሄደው በሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ የአሸናፊውን የፖለቲካ ፓርቲ የምርጫ ውጤት በመቃወም በምርጫው አሸንፎ በሥልጣን ላይ ያለውን የወያኔ መንግሥት በዐመፅና በኃይል ከሥልጣን ለማውረድ እንዲሁም የሕገ መነግሥታዊ ሥርዓትን ተግባራዊነት ለማሰናከል አስበው የተንቀሳቀሱ መሆናቸውን በመግለፅ አቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸው በሰሜን ወሎ ዞን በወልዲያ ከተማ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አባላት ያለ አንዳች ውሳኔ ለሁለት ዓመት ከስድስት ወር ወደ ፍርድ ቤት በመመላለስ መጉላላታቸውን ሰሞኑን ለፓርቲው ጽሕፈት ቤት በላኩት ደብዳቤ ገለጡ፡፡
አባላቱ ቀደም ሲል ሕገ መንግሥቱ ተጥሶ ሶስት ወር ሙሉ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መታሰራቸውን ገልፀው ከዚያን ወዲህም ቢሆን የአቃቤ ሕግ ምስክር እንደሚቀርብባቸው እየተነገረ ለዘጠኝ ጊዜ ወደ ፍርድ ቤት መመላለሳቸውን አምርረው ተናግረዋል፡፡
ተከሣሾቹ አቃቤ ሕግ በውስን ቀጠሮዎች ምስክሮቹን ማቅረብ ካልቻለ ፍርድ ቤቱ ፋይሉን ዘግቶ እነሱን በነፃ ሊያሰናብታቸው ይገባ እንደነበር ገልፀው ይህን ያህል ጊዜ ለአቃቤ ሕግ ዕድል መሰጠቱ ከፍተኛ መጉላላት እንዳደረሰባቸው አስረድተዋል፡፡
በቀጠሮ ብዙ ተጉላልተው እስከ ዛሬ ባንድ ተከሳሽ ላይ አንድ የአቃቤ ሕግ ምስክር ብቻ መቅረቡን የገለፁት ተከሳሾቹ ወደ ፍርድ ቤት በመመላለስ የሥራ ጊዜአቸውን በከንቱ ከማባከናቸውም በላይ በወጪ ረገድ የደረሰባቸውም ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ተከሳሾቹ ባሁኑ ወቅት እነሱን አንገት በማስደፋት ፈርተው ከሕጋዊና ሰላማዊ ትግላቸው እንዲያፈገፍጉ የአገዛዙ ካድሬዎች እንዲሁም ደህንነቶች የሚፈፅሙትን ዛቻ፤ ማስፈራራትና ወከባ በመቋቋም ላይ መሆናቸውን አስረድተው በማያያዝም "እኛ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፖርቲ አባላት የትግላችን ዋንኛ አካል ህግና የሕግ የበላይነት የተከበረበት ሀገር መፍጠር መሆኑን እንገነዘባለን፡፡" ብለዋል፡፡
ከፍተኛ መጉላላት የደረሰባቸው መሆኑን በመግለፅ ለቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ደብዳቤ ከጻፋት የፓርቲው አባላት መካከል ስምንቱ የመንግሥት ሰራተኞች፤ አምሥቱ በንግድ ሥራ የሚተዳደሩ፣ አምሥቱ ደግሞ አርሶ አደሮች ሲሆኑ የተቀሩት ተማሪዎች መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
|