|
ባሁኑ ወቅት ባንዳንድ ክፍላተ ሀገር በቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አባላት ላይ እሥራት፤ እንግልትና ወከባ ተጠናክሮ መቀጠሉን ከልዩ ልዩ አካባቢዎች ሰሞኑን የዓይን ሥምክሮች ገለጡ፡፡
በዚህም መሠረት አቶ ያሬድ ግርማ የሰሜን ጎንደር ዞን የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ኮሚቴ ሰብሳቢ በጎንደር ከተማ በሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ ሐምሌ 8 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም እንዳይነቃነቁ ተደርገው ለግማሽ ሰዓት ታግተው መቆየታቸውን ከሥፍራው የፓርቲው ምንጮች አመለከቱ፡፡
አቶ ያሬድ በቅርቡ በተካሄደው በፓርቲው ጉባዔ በንቃት የተሳተፉ ሲሆን ሊታገቱ የበቁት የመከላከያ ሰራዊት፣ የፖሊስ አባላትና የሥርዓተ-አገዛዙ ደህንነቶች በመስከረም ወር 1998 ዓ.ም ያለ ምንም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከቤታቸው የወሰዷቸውን ሰነዶች እንዲመልሱላቸው ለመጠየቅ ወደ ፖሊስ ጣቢያ በሄዱበት ወቅት መሆኑንም ምንጮች አክለው አመልክተዋል፡፡
እንደ ምንጮች አገላለፅ አቶ ያሬድን ይዘው ያገቷቸው ምክትል ኢንስፔክተር አሥራት ባዬ የሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ መሆናቸው ታውቋል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ አቶ አደይ አንጁሎ በወላይታ ዞን የሶዶ ዙሪያ ወረዳ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ኮሚቴ ሰብሣቢ እንዲሁም በቅርቡ በተካሄደው በፓርቲው ጉባዔ ተሳትፈው የተመለሱት ያለ ምንም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከሐምሌ 6 እስከ 11 ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም ድረስ በሶዶ ፖሊስ ጣቢያ ታሥረው መለቀቃቸውን የዓይን ምስክሮች ከሥፍራው አስታውቀዋል፡፡
አቶ አደይ ከፖለቲካ አንቅስቃሴአቸው አንዲታቀቡ ከሥርዓተ-አገዛዙ አገልጋዮች ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ሲሆን ማስጠንቀቂያውን ገቢራዊ ካለደረጉት ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩበትን ሱቅ እንደሚነጠቁም የተነገራቸው መሆኑን የዓይን ምሥክሮች አክለው አስረድተዋል፡፡
ከመንግሥት ሥራ በፖለቲካ አመለካከታቸው ሳቢያ ተባረሩት አቶ አደይ ከ97 የተወካዮችና ክልል ምክር ቤት አባላት ምርጫ በኋላ ተይዘው ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለሶስት ወራት ታስረው መለቀቃቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚሁ በወላይታ ዞን አቶ መምሩ መደልቾ የኦፋ ወረዳ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴመክራሲ ፓርቲ ኮሚቴ ሰብሳቢ በወረዳው ዋና ከተማ በገሱባ ፖሊስ ጣቢያ ለአንድ ቀን ታስረው በከባድ ማስጠንቀቂያ የተለቀቁ መሆናቸውን የፓርቲው ምንጮች ከወላይታ አመለከቱ፡
አቶ መምሩ በቅርቡ በተካሄደው በፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ወረዳቸውን ወክለው የተሳተፉ ሲሆን ቀደም ሲልም በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ ብዙ መንገላታት የደረሰባቸው ጠንካራ አባል መሆናቸውን የፓርቲው ምንጮች አክለው አስረድተዋል፡፡
በተያያዘ ሁኔታ ወይዘሮ አልማዝ አግደው በወላይታ ዞን የቦምቤ ቦሎሶ ወረዳ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ኮሚቴ ሰብሳቢ በወረዳው ፖሊስ ጣቢያ ለአንድ ቀን ታሥረው መዋላቸውን ሰሞኑን የፓርቲው ምንጮች ከወላይታ አመለከቱ፡፡
ወይዘሮ አልማዝ በቅርቡ በተካሄደው በፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ወረዳቸውን ወክለው የተሳተፉ ሲሆን በወረዳቸው ውስጥ አባላትን በማስተባበር መልካም የሥራ ውጤት ማስመዝገባቸውንም የፓርቲው ምንጮች አክለው አስረድተዋል፡፡
እንዲሁም በዚሁ በወላይታ ዞን በሶዶ ዙሪያ ወረዳ አቶ ወልደ ማርያም ዶላ የዳልቦ ወገኔ ቀበሌ ገበሬ ማህበር የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ኮሚቴ ሰብሳቢ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከሰኔ 1ዐ እስከ ሐምሌ 1ዐ ቀን 2ዐዐዐ ዓ.ም ድረስ ታስረው በማስጠንቀቂየ መለቀቃቸውን ምንጮች ከወላይታ አመለከቱ፡፡
አቶ ወልደ ማርያም ሊታሰሩ የበቁት "በቀበሌው የልማት ሥራ አልተሳተፍክም!" የሚል ሰበብ ቀርቦባቸው ሲሆን ከእሣቸው ጋር ሌሎች አራት ሰዎች ተስረው መፈታታቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
|