|
S3457 እና HR2003 በተመለከተ -
ማስተዋል ያለበት የጋራ የዲፕሎማሲ ሥራ
አማኑኤል ዘሰላም
This e-mail address is being protected from spam bots, you need JavaScript enabled to view it
መስከረም 2 2001
በቅድሚያ በአገር ቤትና ከአገር ዉጭ ለምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ሁሉ እንኳና ለአዲስ አመት በሰላምና በጤና እግዚአብሄር አደረሳችሁ፤ አደረሰን እላለሁኝ።
«መጪዉ ዓመትም በታሪካችን አዲስ ምዕራፍ የሚጀመረበትና በአዲስ አመለካከት በጋራ አገራችን ኢትዮጵያ ካለችበት የድህነት አዘቅት ዉስጥ የማናወጣበት አመት ያድርግልን» እያልኩኝ ለአንባቢያን ለማካፈል የፈለኳቸዉንና ከዉጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ሥራ ጋራ የተገናኘ አንዳንድ ሃሳቦችን በትህትና ለማቅረብ እሞክራለሁኝ።
ሴኔተር ራስ ፋይንጎልድ S3457 ተብሎ የተጠራዉን በኢትዮጵያ ዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብት እንዲከበር የሚጠይቀዉን ረቂቅ ሕግ አቅርበዋል። ሕጉ በብዙ መልኩ በአሜሪካ ህዝብ ምክር ቤት ከአንድ አመት በፊት ካለፈዉ HR2003 ተብሎ ከሚታወቀዉ ረቂቅ ሕግ እምብዛም ባይለያይም መሰረታዊ የሆኑ ጥቂት ልዮነቶች አሉት።
S3457 በአጭሩ
S3457 ሰባት አንቀጾች ሲኖሩት የመጀመሪያዊ አንቀጽ የረቂቅ ሕጉ ስያሜን የያዘ ነዉ። በስያሜዉ «ተጠያቂነት» የሚለዉ ቃል አይጠቀስም። የዲሞክራሲና የሰባዊ መብትን በኢትዮጵያ ለመደግፍ የሚል ብቻ እንጂ።
አንቀጽ ሁለት የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት መስሪያ ቤት ያወጣዉን ዘጋባና የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ያቀረቡትን መረጃዎች በማሰባሰብ በኢትዮጵያ ያለዉን ገጽታና ከዚህ በፊት የተከሰቱ አሳዛኝ ክስተቶችን በሰፊዉ የሚዘግብ ነዉ። እነዚህም አብዛኞቻችን የምናዉቃቸዉና የምንመሰክራቸዉ ብዙም የማያከራክሩ ጉዳዮች ናቸዉ ።
አንቀጽ ሶስት አሜሪካ በኢትዮጵያ ያላትን ፖሊሲ አስታዉሶ አምስት ቁልፍ ነጥቦች ይጠቅሳል። እነርሱን
- ኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ለመገንባትና ጸረ-ሽብረተኝነት ለመዋጋት የምታደርገዉን ጥረት መደገፍ፣
- በኢትዮጵያ መረጋጋት፣ የሕግ የበላይነትና፣ ልማት .. እንዲሰፍን፣
- የታሰሩ የፖለቲካ እሥረኞች ሁሉ እንዲፈቱ፣
- ሰብዓዊ መብትን ለሚረግጡና ግፍን ለሚሰሩ የኢትዮጵያ ሰራዊት ክፍሎችና የደህንነት ኃይላት የሚሰጡ ማናቸዉንም እርዳታ ማገድ (መንግስት ወንጀለኞችን ለፍርድ እስካላቀረበ ድረስ)
- የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮ-ኤርትራን ቦርደር ኮሚሽን የወሰነዉን ዉሳኔ መቀበል እንዳለበት ናቸዉ።
እነዚህ ነጥቦች በአሜሪካ አምባሳደርና በዉጭ ግንኙነት መሥሪያ ቤት ሃላፊዎች በኩል ሁልጊዜ ስንሰማቸዉ የነበሩ በሥራ አስፈጻሚዉም አካል ዘንድም ተቀባይነት ያላቸዉ ብዙም በአሜሪካ ባለሥልጣናት ዘንድ የማያወዛግቡ ናቸዉ ብዬ አስባለሁ።
አንቀጽ አራት ሴኔቱ ሊያስተላለፍ የሚፈልጋቸዉን ስድት አቋሞችን ይዘረዝራል። እነርሱም በአጭሩ የሚከተሉት ናቸዉ፡
- የኢትዮጵያ መንግስት የፖለቲካ እሥረኞችን መፍታቱን በአዎንታዊነት በመመልከት በዚህ ምክንያት የተፈጠረዉን መልካም አጋጣሚን በመጠቀሞ የተሻለ ክንዋኔዎችን ወደፊት ማድረግ እንዲቻል፣
- የኢትዮጵያ መንግስት ለዕርቅ ፋላጎት ካላቸዉ የተቃዋሚ ኃይሎች ጋር ለዉይይት እንዲቀርብ ማበረታታ
- የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎች ሕገ መንግስታዊ መብታቸዉን እንዲያከብር መማጸን
- የሰብዓዊና የስብዓዊ ድርጅቶች የመንቀሳቀስ መብት እንዲጠበቅና ጋዜጠኞች አለተጽኖና እንግልት በየክልሉ መስራት እንዲችሉ ማበረታት
- በሰዎች ሕይወት ላይ ትልቅ ግፍ የፈጸሙትን ግለሰቦችና ድርጅቶች ተጠያቂ ለማድረግ እንዲረዳ፣ የተባበሩት መንግስታም ሆነ ሌሎች አለም አቀፍ ድርጅቶች መረጃ ለማሰባሰብ የሚያደርጉትን ጥረቶች የኢትዮጵያ መንግስት እንዲደግፍና እንቅፋት እንዳይፈጥር
- በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል እርቅ እንዲሰፈን፣ ኢትዮጵያም የድንበር ኮሚሽኑ ያቀረበዉን ዉሳኔ እንድትቀበል (ኢትዮጵያ የድንበር ኮሚሽኑን ተቀበለች ማለት ባድመ ለኤርትራ ተሰጠች ማለት ነዉ )
አንቀጽ አምስት የሴኔቱን አቋም ተግባራዊ ለማድረግ የሥራ አስፈጻሚዉ አካል ሊወስዳቸዉ የሚገባዉን ድርጊቶች ዘርዝሮ ለሥራዉም እንዲረዳ 20 ሚሊዮን ዶላር ባጀት ይመድባል።
አንቀጽ ስድስት ሃያ ሚሊዮን ዶላሩ ለናዛ (የአሜሪካ የጠፈር ምርመራ መሥሪያ ቤት) ተመድቦ ከነበረ ወጪ እንዲወሰድ የሚጠይቅ ሲሆን አንቀጽ ሰባት ደግሞ በረቂቅ ሕጉ ላሉ አንዳንድ አባባሎች ትርጓሜ ይሰጣል።
S3457 እና HR2003 ይለያያሉን ?
በመሰረቱ ሁለቱም ረቂቅ ሕጎች ከላይ በግርድፉ ይለያያሉ እንጂ በዉስጣቸዉ ብዙም ልዩነቶች ያላቸዉ አይመስለኝም። ሁለቱም ረቂቅ ሕጎች ጥርስ ያላቸዉና በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ቀጥተኛ ተጽኖ የሚያመጡ አይደሉም።
እርግጥ HR2003 እንደ ቪዛ መከልከል አይነት ጥርስ እንዳለ የሚያስመስሉ አንዳንድ እገዳዎችን ይዘረዝራል። ነገር ግን እነዚህ እገዳዎች ቢዘረዘሩም ቅሉ ተጋብራዊ ሊሆኑ የማይችሉና በቀላሉ በሌላ አማራጭ መንገዶች የሚጣሱ ናቸዉ ብዬ አስባለሁ።
አንዳንድ የዚህን ሕግ ጥቅም ከመጠን በላይ የለጠጡ ቡድኖች HR2003 ጥርስ እንዳለዉ አድርገዉ በማቅረብ ሕዝባችንን ሲያወናብዱት እንደነበረ የምናስታዉሰዉ ነዉ። ነገር ግን HR2003 የፕላስቲክ ጥርስ አድርጎ ስለነበረ ጥርስ እንዳለዉ ተደርጎ በስህተት ተወሰደ እንጂ ጥርስ አልነበረዉም። «ከHR2003 ዙሪያ ያሉ ግራ ማጋባቶች» በሚል አርዕስት ያቀረብኩት ጽሁፍ እንዴት HR2003 ጥርስ እንደሌለዉ በግልጽ ለማሳየት ሞክሪያለሁ)
ሁለቱም ረቂቅ ሕጎች ሃያ ሚሊዮን ዶላር ለዲሞክራሲ ግንባታ ለኢትዮጵያ ይመድባሉ። ሁለቱም በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ግንባታዉ ሂደት ሃዲዱን ስቶ እያሽቆለቆለ እንዳለ በግልጽ አስቀምጠዋል። ሁለቱም በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ያለዉ ግንኙነት በጣም ቁልፍ እንደሆነና የበለጠ መጠናከር እንዳለበት አስምረዉበታል።
ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ረቂቅ ሕጎቹ የሚመሳስላቸዉ ብዙ ነጥቦች ቢኖሯቸዉም በቁጥር የማይናቁ ልዩነቶችም አሏቸዉ። ከነዚህም ልዩነቶች ዉስጥ ስድስቱን ብቻ እንደ ክብደታቸዉ ደረጃ ለመጠቆም እሞክራለሁኝ።
- HR2003 ስለ ኤርትራ ብዙም አልጠቀሰም። S3457 ኢትዮጵያ የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ኮሚሽን የወሰነዉን ዉሳኔ ኢትዮጵያ እንድትቀበል ይጠይቃል። በሌላ አባባል የብዙ ወጣቶቻችን ደም መፍሰስ ምክንያት የሆነችዉ ባድመ ለኤርትራ እንድትሰጥ ነዉ ረቂቅ ሕጉ የሚጠይቀዉ።
- ይህ መሰረታዊ ችግርን የሚፈጥር፣ እንዳለ ረቂቅ ሕጉ በኢትዮጵያዉያን ዘንድ እምብዛም ተቀባይነት እንዲያጣና የተቃዋሚ ፓርቲዎችም እንዳይደግፉት ሊያደርግ የሚችል በጠቃሚ አንቀጾች ዉስጥ የተተከለ መርዝ አድርጌ አየዋለሁኝ።
- የድንበር ኮሚሽኑን የአልጀርሱ ስምምነት ነዉ የወለደዉ። የአልጀርሱ ስምምነት ደግሞ ያለ ሕዝብ ፍቃድ ኢሕአዴግ የወሰነዉ ጸረ-ኢትዮጵያ ዉሳኔ ነዉ። በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌለዉ ከመሆኑም ባሻገር ባድመ ሙሉ ለሙሉ የኢትዮጵያ ግዛት መሆኗ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም። (እንደዉም እራሷ ኤርትራ የኢትዮጵያ ናት በታሪክና በሕግ አኳያ ከተወሰደ።)
- HR2003 የኢትዮጵያን መንግስት በበለጠ የተጫነ የሚመስልና ላይ ላዩን ኃይለኛ እንደሆነ ተደርጎ የሚቆጠር ረቂ ሕግ ነዉ። S3453 በአንጻሩ በዉስጣዊ ተግባራዊ ይዘቱ እምብዛም ከHR2003 ባይለይም የኢትዮጵያ መንግስት የበለጠ ወደ ቀናዉ መንገድና እርቅ እንዲመጣ መምከሩና ማበረታታቱ ላይ ያተኮረ ይመስላል። ሁለቱም ረቂቅ ሕጎች አላማቸዉና ይዘታቸዉ አንድ ሆኖ እያለም አቀራረባቸዉና ቶናቸዉ የተለያየ እንደሆነ እናያለን።
- ለዚህም ነዉ በሴነቱ ረቂቅ ሕግ ላይ በርካታ ጊዜ "እናበረታታለን" የሚል ቃል የምናነበዉ። ለዚህም ነዉ በ2003 እንደምናየዉ «ይህን ካላደረጋችሁ ይሄ ይከተላል» የሚሉ የማስፈራሪያ ሃረጎች በS3453 ዉስጥ የማናነበዉ።
- S3457 በተለየ መልኩ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የአገሪቱን ሕግ ይጋፋል ተብሎ በማያስፈርጅ መልኩ የቀረበ ነዉ። ብዙዎቻችን እንደምናስታዉሰዉ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት HR2003 እንደ ዉጫሌ ዉል ቆጥረዉ፣ አሜሪካ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ጣልቃ እየገባች እንደሆነ ሲናገሩ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንዴት ኢትዮጵያ የራሷ ሕግ አዉጪ አካል እያላት የሌላ አገር ሕግ አዉጪ አካል በኢትዮጵያ ላይ ሕግ ያወጣል ብለዉ በፓርላማ ንግግራቸዉ HR2003 ለማጣጣል የተናገሩትን አስታዉሳለሁ። ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያልተረዱት ወይንም አማካሪዎቻቸዉ በደንብ ያላስረዷቸዉ ነገር ቢኖር HR2003 በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ አሜሪካ ጣልቃ እንድትገባ የሚጠይቅ ረቂቅ ሕግ ሳይሆን አሜሪካኖች በራሳቸዉ ገንዘብና በራሳቸዉ አገር ጉዳይ ላይ የወሰኑት ዉሳኔ ነዉ። (ስለ ኢትዮጵያ ሕጉ ቢናገርም አሜሪካ ለኢትዩጵያ ስለምትሰጠዉ የራሷ ገንዘብና ኢትዮጵያዉያን ወደ አሜሪካ ሲመጡ ማን ቪዛ ይሰጠዉ የሚለዉን ነዉ ሕጉ የዳሰሰዉ)
- አሜሪካኖች የራሳቸዉን ገንዘብ በፈለጉት መልኩ የማደላደልና ማን አገራቸዉ መግባት እንዳለብት የመወሰን ሙሉ መብት እንዳላቸዉም የኢሕአዴግ ባለስልጣናት ያጡታል ብዬ አላስብም።
- የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት በማይታሰብና በማይዛመድ መልኩ ለጥጠዉት በመተርጎም HR2003ን እንዳጠቁ ከግምት ዉስጥ በማስገባት ይመስለኛል፣ በአንቀጽ አምስት መጀምሪያ አረፍተ ነገር ላይ ፣ የዲሞክራሲ፣ የሰብአዊ መብት መከበርና መልካም አስተዳደር በኢትዮጵያ ይሰፋ ዘንድ፣ በረቂት ሕጉ የተዘረዘሩት ነጥቦች በኢትዮጵያ ያለዉን ሕገ መንግስት በጠበቀ መልኩ ለማስፈጸም እንዲሞከር S3457 በግልጽ ያስቀመጠዉ።
- S3457 የኢትዮጵያን ሕገ መንግስት ሆነ የአገር ሉዓላዊነት የሚጻረር ሕግ አይደለም። ነገር ግን ኢትዮጵያ አንድ እርምጃ እንድትራመድ ለመርዳት የሚሞክር በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር ለማገዝ የረቀቀ ሕግ ነዉ።
- HR2003 ከመንግስት ዉጭ በሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች የተሰሩ ግፎችን አላቀረበም። S3452 ግን ሚዛናዊነት ይታይበታል። የኦጋዴን ነጻ አዉጭ ግንባር በሰላማዊ ዜጎች ላይ የፈጸመዉንና እየፈጸመ ያለዉን ሽብር የሴኔቱ ረቂቅ ሕግ ዘግቦታል። የዉጭ ግንኙነት መሥሪያ ቤትን በመጥቀስ በS3453 በአንቀጽ ሁለት ንዑስ አንቀጽ 10 ኦብነግ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት እንዳደረገ ነዉ የምናነበዉ።
- HR2003 እንዲሁም S3457 ሃያ ሚሊዮን ዶላር ለዲሞክራሲ ግንባታ ባጀት የመደቡ ሲሆን HR2003 በግልጽ ሲቪክ ማህበራትና የፖለቲካ ድርጅቶች ከዚህ ገንዘብ ድጋፍ እንደሚያገኙ ጠቅሷል። S3457 ብዙም የገንዘቡ አጠቃቀም ሁኔታ ላይ የሰጠዉ ትንታኔ የለም።
ከአሁን በኋላ ወዴት ?
S3457 በሴኔት ዉስጥ ብዙ ተቃዉሞ የሚገጥመዉ አይመስለኝም። ብዙ አከራካሪና አወዛጋቢ ነጥቦች የሉበትም። ድንገት 20 ሚሊዮን ዶላር ከናዛ ባጀት መዉጣቱን የሚቃወሙ ሴኔትሮች ካሉ በገንዘቡ ምክንያት ችግር ካልተፈጠረ በቀር የአሜሪካን ሴኔትን በቀላሉ በቅርብ ጊዜ ዉስጥ ሊያልፍ የሚችል ነዉ ብዬ አስባለሁኝ።
በዚህ አጋጣሚ ብዙ እንደሰይጣን ሲደበደቡ የነበሩትና ከሁለት ወር በኋላ በሚደረገዉ ምርጫ ተቀናቃኛቸዉን ከ20 ነጥብ በላይ በሕዝብ አስተያየት እየመሩ ያሉ የኦክላሆማዉ ሴኔትር ኢንሆፍም ሊደግፉት የሚችሉት ረቂቅ ሕግ እንደሆነ አስባለሁ።
የግጭት ፖለቲካን ከማራገብ በአክብሮት እኝህንና ሌሎች ሊቃወሙ ይችላሉ የሚባሉትን ሴኔተሮች በማስተዋል መቅረብና ማነጋገር ከቻልን ብዙ ልንደነቅ እንችላለን።
S3457 በሴኔት ከጸደቀ በኋላ ከሴኔትና ከሕዝብ ምክር ቤት የተወጣጡ HR2003 እና S3457 ለማስታረቅ ይሞክራሉ። ከዚያም ሁለቱም የሕግ አዉጪ ክፍሎች የተስማሙበት አንድ የጋራ ሕገ ረቂቅ ይዘጋጅና ድምጽ ተሰቶበት ለፕሬዘዳንቱ ፊርማ ይሄዳል።
የጋራ ረቂቅ ሕጉ በS3457 ካለዉ ጋር የበለጠ ሚጠጋጋ ከሆነ የአሜሪካ የሥራ አስፈጻሚ አካልም እንደሚደግፈዉ ነዉ። ስለሆነም ፕሬዘዳንቱ በቀላሉ ይፈርሙታል ብዬ አስባለሁ።
S3457 ከሕዳር ወር 2001 መጨረሻ በሙሉ ሴኔት ዉስጥ ድምጽ ካልተሰጠበት HR2003 ይሞታል። ከጥር በኋላ እነ ኮንግረስማን ዶናልድ ፔን እንደገነ ተመሳሳይ ሕግ ማዉጣት ይኖርባቸዋል ማለት ነዉ። ያኔ ፕሬዘዳንቱ ሴኔተር ኦባማ ወይንም ሴኔተር ማኬን ነው የሚሆኑት። ራስ ፋይንጎልድ በሴኔተር ማኬን በጣም ተሰሚነት ስላላቸዉ (አብረዉ በርካታ አበይት ሕጎችን እንዲወጣ አብረዉ የሰሩ ናቸዉና) ሴኔተር ኦባማ ደግሞ እንደ ሰኔተር ፋይንጎልድ ዴሞክራት ስለሆኑ ይህ ረቂቅ ሕግ በመጪዉ የአሜሪካ አስተዳደርም ችግር የሚያጋጥመዉ አይመስለኝም።
የኛ የኢትዮጵያዉያን ድርሻ ምንድን ነዉ ?
በመጀመሪያ ደረጃ ሁላችንም የዚህን ረቂቅ ሕግ መንፈስ መረዳት አለበን። ሕጉ አሁን በኢትዮጵያ ያለዉን መንግስት ለመቅጣት የረቀቀ ሕግ አይደለም። ሕጉ አሁን ያለዉን መንግስት እንደ አጋር የሚያይ ሕግ ነዉ። ሕጉ የኢሕአዴግ ባለስልጣናት አላወቁትም እንጂ ኢሕአዴግን እራሱ የሚጠቅም ሕግ ነዉ። የዚህ ሕግ አላማ በኢትዮጵያ እያንዳንዱ ዜጋ መብቱ ተከብሮ፣ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ተጠብቆ ኢትዮጵያ ካለችበት አዘቅት እንድትወጣ የሚያግዝ ሕግ ነዉ። በኢትዮጵያ እርቀ ሰላም እንዲመጣ የሚያበረታታ ሕግ ነዉ።
በሁለተኛ ደረጃ ኢትዮጵያን የሚጠቅም ረቂቅ ሕግ ሲወጣ በኛ በኩል ማድረግ ያለብንን ሁሉ በጥንቃቄና በማስተዋል ማድረግ ይጠበቅብናል። ዲፕሎማሲ ወይንም የዉጭ ግንኙነት ሥራ በስሜት፣ በእልህ ወይንም በሜዲያ ፕሮፖጋንዳ የሚሰራ አይደለም። ከቀድሞ አባቶቻችን ከነ አምባሳደር እምሩ ዘለቀ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሃብተወልድ የምንማራቸዉ ብዙ ጥበቦችና ዘዴዎች አሉ። የአሜሪካ የፖለቲካ ሳይንስ መጽሃፍትን ለጊዜዉ ትተን ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል ከስድሳ አመታት በፊት በአምባሳደሮቻችን በኩል ሲደረግ የነበረዉን ታሪክ መለስ ብለን ብናጠና ብዙ እንማር ነበር።
በተለይም HR2003-ኮአሊሽን እየተባለ የሚታወቀዉ ቡድን እያደረገ ያለዉ እንቅስቃሴ ብዙም አይጥመኝም። ይህ ቡድን መግለጫዎችን በሜዲያ እያወጣ ፣ ኢትዮጵያዉያን አላስፈላጊ ፋክሶች፣ ወረቀቶች እንዲልኩና የሴኔተሮችን ሰራተኞች በባዶ የማድከም ሥራ ነዉ እንዲሰራ ነዉ ሲያደርግ የነበረዉ። አንድ ወቅት ለምሳሌ ለ100 ሴኔተሮች HR2003ን እንዲደግፉ ፋክሶችና ኢሜሎች ለወራት ሲላክ እንደነበረ አስታወሳለሁ። ለፕሬዘዳንት ጆርጅ ቡሽ ከአሥር ገጽ በላይ የሆነ ሰነድ ከመቴ ሺህ በላይ ኢትዮጵያዉያን ፋክስ እንዲያደር የሚጠይቅ ዘመቻ እንደነበረ አስታዉሳለሁ። እግር ኳስ ለመጫወት የቴኒስ ራኬት ይዞ መምጣት !
የሎቢና የዲፕሎማሲ ሥራ የሚሰራዉ በጥንቃቄና በማስተዋል ነዉ። ኢትዮጵያዉያን እንደ ሜክሲኮዎች ወይንም ይሁዶች ብዛትና የገንዘብ አቅም ያለን አይደለንም። የHR2003-ኮአሊሽን ዘዴ የሚሰራዉ ለእንደዚህ አየነቱ ኮሚኒቲዎች ነዉ።
አሁን HR2003-ኮአሊሽን እንዳደረገዉ ሴኔተሮችን በመጨቅጨቅና በመጫን ደብዳቤዎች በብዛት ፋክስ በማድረግ ወደኛ ልናመጣቸዉ አንችልም። እዉነታዉ ይሄ ነዉ። ስለዚህ ወደድንም ጠላንም የነርሱን መልካም ፈቃደኝነት ማግኘት ካልቻልን የትም አንደርስም።
HR2003 ሕግ የሆነዉ እነ ኮንግረስማ ክርሲ ስሚዝና ዶናልድ ፔን አይነት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተቆርቋሪ ሰዎች ስላገኘን ነዉ። (አንድ ወቅት እንደዉም ዶናልድ ፔንንም የምንሳደብ ሰዎች ነበርን)
ሴኔተር ፋይንጎልድ S3457ን ሲያረቁ በዉስጣቸው የኢትዮጵያ ጉዳይ ስላሳሰባቸው ነዉ። ኢትዮጵያን የጎበኙ ሲሆን በርካት ጊዜ በሴኔት ዉስጥ ስለኢትዮጵያ ንግግር አድርገዋል። ያለፈዉ አመት ከአሥር በላይ ሴኔተሮችን በማስተባበር እስረኞች እንዲፈቱ የጋራ ጥሪ ያደርጉ ሰዉ ናቸዉ።
አብረዋቸዉ የዚህ ሕግ ስፖንሰር የሆኑት ሴኔተር ፓትሪክ ሌሂም በዚያ አካባቢ ያሉ ስማቸዉን የማናዉቃቸዉ ኢትዮጵያዉያን ከወዲሁ በየጊዜዉ የኢትዮጵያን ጉዳይ ስለሚያስረዷቸዉ በሥራ ኢትዮጵያም ባይሄዱም በልባቸዉ ኢትዮጵያን የሚያዉቁና የሚወዱ የተከበሩ ሰዉ ናቸዉ።
በብዛት ፋክስ ስለተደረገላቸዉ ወደፊት እንዳይመረጡ የኢትዮጵያዉያንን ድምጽ ስለፈሩ አይደለም ዶናልድ ፔን ክርሲ ስሚዝም ፓትሪክ ሌሂና ራስ ፋይንጎልድ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ረቂቅ ሕግ ያወጡት። ነገር ግን ለሰብዓዊ መብት ትልቅ ቦታ ስለሚሰጡና ኢትዮጵያን ስለሚወዱ እንጂ።
ታዲያ ኢትዮጵያን የሚወዱትን ለማብዛት ትሁት፣ ትዕግስተኛ መሆንን ይጠይቃል። ዛሬ እኛን ባይደግፉ ታግሰን ሁሉን በሆዳችን ይዘን ነገ ወደኛ እንዲመጡ መጣር ነዉ የሚያስፈልገዉ። ብንሰድባቸዉ፣ ብናጋልጣቸዉ፣ ብናኮርፋቸዉ፣ ብናብጠለጥላቸዉ የትም አንደርስም። (ሴኔተር ኢንሆፍን አንመለከትም- ይኸዉ በብዙ ድምጽ እንደገና ይመረጣሉ ተብሎ ነዉ የሚጠበቀዉ። እንደዉም እርሱን ማጥቃቱ ላይ ከምናዘነብል በትዕግስት ወደኛ ለማምጣት ብንሞክር ይሻል ነበር)
ለማጠቃለል የወደፊት ጉዙዋችንን ይረዳ ዘንድ የሚከተሉትን ሃሳቦች አቅርቤ አቆማለሁ።
- S3457 ሕግ ከመሆኑ በፊት መስተካከል ያለባቸዉን ነጥቦች (ለምሳሌ የኤርትራን ጉዳይ ከረቂ ሕጉ ስለማስወጣት) የሚመክርና በጥንቃቄ የሴኔተር ራስ ፋይንጎልድ ጽ/ቤት ጋር ግንኙነት ፈጥሮ የሚሰራ ግብረ ኃይል በአስቿኳይ ያስፈልገናል። HR2003-ኮአሊሽን ከዚህ በፊት ሲያደርግ እንደነበረዉ ይህ ጉዳይ የሜዲያ ወይንም የፕሮፖጋንዳ ጨዋታ አይደለም።
በርካታ በዲፕሎማሲ የተካኑ አዋቂ ኢትዮጵያዉያን አሉ። አምባሳደር የነበሩ፣ የሕግ ሰዎች፣ የፖለቲካ ሳይንስ ጠበብት፣ በዋሺንግተን ዲሲ ደግሞ በካፒታል ሂል የሴኔት ሰራተኞችን የሚያዉቁ ብዙ አሉ። እነዚህ ተለይተዉ ፕሮፌሽናል በሆነ መልኩ ሥራዉ እንዲሰራ ቢደረግ መልካም ነዉ። (ከሜዲያዉ ፕሮፖጋንዳ ዉጭ ዉስጥ ለዉስጥ የሚሰራ ሥራ ማለቴ ነዉ።)
የአንድነት የድጋፍ ድርጅት የዲፕሎማሲ ኮሚቴ፣ ዋሺንግተን ዲሲ የሚገኘው የኢትዮጵያን አሜሪካን ሲቪክ አድቮከሲ ግሩፕ፣ አቶ መስፍን መኮንን የሚመሩት የመኢአድ ድጋፍ ድርጅት የዉጭ ግንኙነት ኮሚቴ፣ HR2003-ኮአሊሽን፣ የአኝዋክ ጀስቲስ ካዉንስል፣ የኢትዮጵያ ሶሊዳሪቲ ፎረም፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጉባዔ እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ለዉጥ ሊያመጡ የሚችሉ እንደ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ አይነቶቹ በአንድ ላይ ሆነዉ ለጅምሩ ያህል ይህ ሕግ የሚሻሻልበትን ሁኔታ ቢሰሩ እንደ አንድ ጊዚያዊ አማራጭ መልካም ሊሆን ይችላል።
- ኢትዮጵያዉያን በየስቴቱ ያሉ የሴኔተሮቻቸዉን ሰራተኞች ከወዲሁ መቅረብና ያለዉን ሁኔታ ማስረዳት ይጠበቅብናል። የሴኔት ረቂቅ ሕግ ስላለም ይህን ሕግ ኮስፖንሰር እንዲያደርጉ የመጠየቅ ሥራ በተቀናጀና ስሜታዊ ባልሆነ መንገድ መሰራት መጀመር አለበት።
- የዚህን ሕጋ አላማ ካለመረዳት የተነሳ S3457ን የሚቃወሙ የኢሕአዴግ ደጋፊዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ለነዚህ ያለኝ መልእክት S3453ን በእርጋታ እንዲያነቡት ነዉ። ነገር ግን እንዲሁ በጭፍን ፖለቲካ መቆየቱ የወደዱ ከሆነ በዚህ ረቂቅ ሕግ ላይ ጥቃታቸዉን ሊሰነዝሩ ይችላሉ። ስለዚህም ይህን ተረድተን በእነርሱ ዘንድ ለሴኔተሮቹ ሊቀርቡ የሚችሉትን ተቃራኒ ሃሳቦች ዉድቅ ለማድረግ በስሜት ላይ ሳይሆን በመረጃ ላይ የተመሰረተ መከራከሪያዎች ማቅረብ ይጠበቅብናል።
|