|
ከመሳፍንት ዘፈረንሳይ ለጋሲዮን (አዲስ አበባ)
(
This e-mail address is being protected from spam bots, you need JavaScript enabled to view it
)
ሚያዝያ 2001 ዓ.ም
በታሪክ የምናዉቃት ሳትሆን በእድሜያችን ያየናት ኢትዮጵያ ገዢዎቿ ችግሮቿን ያስቆጠሩላት ግን ያልቀነሱላት፣ የተወቃቀሱባት ግን ያልተማማሩባት፤ ህዝቦቿም ሰላምንና ብልፅግናን የሚመኙላት ግን ያላዩባት ሀገር ናት፡፡ በየጊዜያቱ "መፍትሄሽ በእጄ ነዉ" እያሉ የተቀባበሏት መንግስታት እየተጓዘችበት ያለዉን የቁልቁለት መንገድ ማብቂያ የሌለዉ እስኪመስል አርዝመዉባታል፡፡ ላለፉት 18 ዓመታት እጁ ላይ ያኖራት ባለተራ ምድሯን ለሰላም፣ ኢኮኖሚዋን ለእምርታ፣ ሕዝቦቿንም ለእኩልነት አብቅቼላታለሁ እያለ የሚናገርላት ሀገራችን በአንፃሩ እዉነታዎቿ ሰምጣ የምትገኝበትን የአዘቅት ውቅያኖስ ቁልጭ አድርገዉ ያሳዩናል፡፡
ኢትዮጵያ ዛሬም ስሟ ከረኃብ መዝገብ ሊፋቅ አልቻለም፡፡ ገዢዋ ከአንደበቱ ባወጣዉ አሀዝ መሰረት እንኳን ከ5 ሚሊዮን የማያንስ ሕዝባችን አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እየጠበቀ ነዉ፡፡ ድህነትም እንደዛዉ ቤቱ እኛ ዘንድ ነዉ - ከ80 በመቶ የማያንሰዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ የዕለት ገቢዉ ከሁለት ዶላር አይበልጥም፡፡ "በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ" እንዲሉ የኑሮ ዉድነቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ በፍጥነት እያሻቀበ ነዉ፡፡ የኑሮ ደረጃ ልዩነቱስ? 40 በመቶ የሚጠጋዉ የሀገሪቱ ሀብት የሚገኘዉ ከሕዝቧ 1 በመቶ በማይበልጡ የገዢዉ አገልጋይ ወይም ባለሟል በሆኑ ባለሀብቶች እጅ ነዉ፡፡ ሙስናና የሀገር ሀብት ዘረፋ ከወንጀል እንደማይቆጠሩ ሁሉ በአደባባይ የሚፈፀሙ ሆነዋል፡፡ ስራ አጥነት ሌላው የሀገሪቱ ራስ ምታት ነዉ፡፡ የኢህአዴግ መንግስት ሽባ ፖሊሲዎች እጅግ በርካታ ትምህርት/ስራ አጥ ወጣቶችን ፈጥረዋል - "አደገኛ ቦዘኔ" የሚባሉ፡፡ ሰራተኛውም ከስራ ያለመባረር ዋስትና (Job security) የለዉም - ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ ያለማቋረጥ የምንሰማዉ "የሰራተኛ ቅነሳ" ዜና የሚያስረግጠዉ ይህንኑ ነዉ፡፡ ስደት ሌላዉ መገለጫችን ነዉ - ባለፉት 18 ዓመታት ከሀገሩ የተሰደደዉን ሕዝብ ቤቱ ይቁጠረዉ፡፡
ኢትዮጵያ በሰብዐዊ መብት አከባበር ረገድም ስሟ ጥቁር ነዉ፡፡ ገዢዋ "የብሄር ብሄረሰቦችን መብት አስከብሬባታለሁ" በሚልባት ሀገር የነጻ አዉጪ ድርጅቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ነዉ፡፡ "Genocide Watch" የተሰኘ ዓለም አቀፍ ድርጅት በቅርቡ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያቀረበዉ ማስረጃ የሚያረጋግጠዉ የኢትዮጵያ መንግስት እየፈፀመ ያለዉን የዘር ማጥፋትና የሰብዐዊ መብት ረገጣ እንጂ በኢህአዴጋዉያን ሌት ተቀን የሚነበነበዉን "እኩልነት" አይደለም፡፡ ሰዎች በፖለቲካ አመለካከታቸዉ ወከባና እንግልት፣ እስር ብሎም ግድያ ሲፈፀምባቸዉ ማየትና መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ ኢህአዴግ ራሱ ቀርፆ ራሱ ላፀደቀዉ ሕገ-መንግስት ተገዢ አይደለም - ይልቁንም ሕገ-መንግስቱ ሕዝብን እንደፈለገ ሲያንገላታ የሚለብሰዉ ካባ ሆኖለታል፡፡
ጦርነትና የርስ በርስ ግጭት ዛሬም የሀገራችንን ገፅታ ይመሰክራሉ፡፡ በዘመነ ኢህአዴግ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በብሄሮችና በጎሳዎች መካከል ቁጥራቸዉ ቀላል የማይባል ግጭቶች ተከስተዋል፤ እየተከሰቱም ነዉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሀገሪቱ በየአቅጣጫዉ ከዉጭም ሆነ ከዉስጥ ሃይሎች ጋር ተደጋጋሚ ጦርነት ዉስጥ ገብታለች፡፡ ለአብነት ኢህአዴግ በኦሮሚያና በኦጋዴን ከነፃ አዉጪ ሃይሎች ጋር የሚያካሂዳቸዉ ማለቂያ የሌላቸዉ ጦርነቶች ይጠቀሳሉ፡፡ ሶማሊያ ዉስጥ ላለፉት ሁለት ዓመታት አላስፈላጊ በሆነና ይህ ነዉ የሚባል ውጤት ባልተገኘበት የውክልና ጦርነት ውስጥ ስንዳክር ቆይተናል፡፡ በሰሜንም ከኤርትራ ጋር ብዙዎችን የጨረሰና አሁንም ከዛሬ ነገ ይነዳል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሻዉ የሚራገብ አሊያም የሚዳፈን የጦርነት ፍም አለ፡፡ በነዚህ ከዉስጥና ከዉጭም በተከሰቱ ግጭቶች በርካታ ዜጎች ለህልፈተ-ህይወት አልያም ከቄያቸዉ ለመፈናቀል፣ ሕዝቦች ለአላስፈላጊ ቁርሾ እንዲሁም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ለድቀት ተዳርገዋል፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያችን የተተበተበችባቸዉ ችግሮች ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆኑ የግዛት አንድነት አደጋንም የሚጨምሩ ናቸዉ፡፡ ሀገራችን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ መሬቷን ለጎረቤቶቿ እንደቡና ቁርስ እየቆረሰ የሚያድል መንግስት አግኝታለች፡፡ የራሱን ጥቅምና የስልጣን እድሜ ብቻ ታሳቢ እያደረገ የሚጓዘዉ የኢህአዴግ መንግስት ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ዘለቄታ የሌለዉ ወዳጅነትን ለመፍጠር ወይም አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚሞክረዉ የሀገሪቱን መሬት በመገበር ነዉ፡፡ በዚህም የሀገሪቱ ሉዓላዊነት ጥያቄ ዉስጥ ገብቷል፣ ጎረቤቶቿም "ኢትዮጵያ" የምትባለዉን ሀገር ራሷን የማትጠብቅና ደካማ አድርገዉ ስለዋታል፡፡ በቂ ጥናት ሳይደረግባቸዉ በአጭር ጊዜ የጥቅም ማስከበሪያነት ላይ ብቻ በመመስረት የተቀረፁት የዉጭ ግንኙነት ፖሊሲዎች የሀገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም፣ ተሰሚነትና ክብር በእጅጉ ጎድተዋል፤ የዉጭ ግንኙነት ሚናዋንም ከታዛዥነት ያላለፈ አድርገዉታል፡፡
ዉድ ወገኖቼ፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እምርታ እያሳየ ነው፣ ሀገራችን የእኩልነት ቤት ሆናለች ወዘተ ወዘተ በሚል እንደሚስተጋባዉ የኢህአዴግና ደቀመዛሙርቶቹ ፌዝ ሳይሆን የዛሬዋ ኢትዮጵያ ከላይ ለአብነት በተጠቀሱትና በሌሎችም በርካታ ችግሮች የተተበተበች ሀገር መሆኗ ከማንኛዉም ኢትዮጵያዊ የተሰወረ አይደለም፡፡ ሰምጠን ለቀረንበት ዉድቀት ሀገራችንን ለዘመናት ጠፍሮ ከያዛት ብልሹ አስተዳደር በተጨማሪ እኛ ዜጎቿ ያደረግነዉና ያላደረግነዉ ሁሉ ድርሻ አላቸዉ - የተበታተነና ወጥነት የሌለዉ ትግል ስናራምድ መቆየታችን፣ የሀገራችንን ጉዳይ ዳር ቆመን ለመመልከት መምረጣችን፣ በጋራ ጉዳዮቻችን ላይ መግባባት አለመቻላችን፣እንዲሁም የኢህአዴግን ባህሪ በቅጡ አለመረዳታችን ከችግሮቻችን መሀል ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡
ኢትዮጵያ የህዝቦቿ የጋራ ቤት እንደመሆኗ ችግሮቿም የጋራችን ናቸዉ፡፡ የዛሬዉ አገዛዝ ዕድሜዉ እንዲህ እንደዋዛ የረዘመዉ በድርጅቱና ዉስጡ በተሰገሰጉት ሰዎች ጥንካሬ ሳይሆን እኛ በየፊናችን ለመጓዝ በመምረጣችን ነዉ፡፡ ወቅቱ ተቃዋሚዎች የአመለካከት ልዩነታቸዉን በማጥበብ፤ ግለሰቦችን ሳይሆን ሀገርን በማስቀደም በጠራ የትግል መስመር ተሰባስበው አባላትና ደጋፊዎቻቸዉን ዉጤት ሊያስገኝ በሚችል እንቅስቃሴ ዉስጥ እንዲያሳተፉ ያስገድዳል፡፡ የአንዱን ኢትዮጵያዊ ወይም የኢትዮጵያ ክፍል ችግር ከሌላው ለይቶ ማየትና ለመፍታት መሞከር የትም አላደረሰንም፣ አያደርሰንምም፡፡ መሰረቱ ሕብረ-ብሄር የሆነ እንደ ኢትዮጵያ ያለ ሕዝብ ችግሮቹን ቀርፎ ለእድገትና ለብልፅግና ሊበቃ የሚችለዉ አብሮ መክሮ አብሮ መስራት ሲችል ብቻ ነዉ፡፡
በጋራ ለመታገል የገዢያችንን ባህሪ ማወቅም የግድ ነዉ፡፡ ኢህአዴግ ራሱ ቀርፆ ባፀደቀዉና "መተዳደሪያዬ" በሚለው ሕገ-መንግስት ዉስጥ የሀገሪቱ የፖለቲካ ስርዓት ህልዉና በሕዝብ ይሁንታ ላይ ብቻ የፀና እንደሚሆን አመላክቷል፡፡ ይኽዉ ህግ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች እሱኑ ተገን አድርገዉ በሀገሪቱ ፖለቲካ ዉስጥ ተሳታፊ ለመሆን ሞክረዋል፤ ዛሬም እየሞከሩ ነዉ፡፡ በአሁኑ ወቅት እንኳን በሀገሪቱ የምርጫ ቦርድ የተመዘገቡ ከ80 በላይ የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ኢህአዴግ በአንድ ወገን በሀገሪቱ ያለዉ የፖለቲካ ምህዳር ህጋዊ የትግል መድረኮችን የሚያበረታታ ነው በማለት እየደሰኮረ፤ በሌላ ወገን የፓርቲዎችን እንቅስቃሴ በቢጫና ቀይ ቀለማት ተከልለዉ በጠበቡ "ህጋዊ መንገዶች" ዉስጥ ወስኖታል፡፡ የፓርቲዎችን ራዕይ፣ ጥንካሬና በሕዝብ ዘንድ ያላቸዉን ወይም ሊኖራቸው የሚችለዉን ተቀባይነት በማጤን አባላትና ደጋፊዎቻቸዉን በማዋከብና ወህኒ በመዶል ሲያሰኘዉም በመግደል ትግላቸዉን ሲያሰናክል፣ ሕዝቡንም ተስፋ ለማስቆረጥ የቻለዉን ሁሉ ሲያደረግ አይተናል፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት የአብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴም ቢሆን ወጥነት የሌላዉና የኢህአዴግን ማንነት ግንዛቤ ዉስጥ ያላስገባ በመሆኑ የጉዟቸዉ መብራት ሳይበራ ሲጠፋ በተደጋጋሚ ተስተዉሏል፡፡ ይህም የገዢዉን ልብ ሰዉሮ "ለጠንካራ የተቃዋሚ ፓርቲ አልታደልኩም" በማለት እስከመሳለቅ እንዲደርስ አድርጎት ነበር፡፡
ገዢዉ ፓርቲ በተሳሳተ ስሌት በገባበት የ1997 ዓ.ም ምርጫ ልኩን ካየ በኃላም ሕዝቡ በፍርሀት እንዲዋጥና በተቃዋሚዉ ትግል ላይ ተስፋ እንዲያጣ ያገኝዉን ድንጋይ ሁሉ መፈንቀል ይዟል፡፡ እንደለመደዉ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ከማዋከብ፣ ከማሰርና ብሎም ከመግደል በተጨማሪ ፓርቲዎችንና ህዝቡን የሚያገናኙ መንገዶችን አንድ በአንድ መዝጋትና የሕዝብ መሆን ያለባቸዉን ተቋማትም የራሱ አገልጋዮች ማድረግ ተያይዟል። በተጓዳኝ ተለጣፊ እና ደካማ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማራባት በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ ያለ በማስመሰል ሌሎችን ለማጭበርበር ወጥሮ እየሰራ ነዉ፡፡ ሕዝቡ የፓርቲዉ አባል እንዲሆን የተለያዩ ጫናዎች እየተደረጉበት ነዉ፡፡ ዛሬ የኢህአዴግ አባል ሳይሆኑ ስራ፣ ከፍተኛ ትምህርትና ሌሎች መሰል ዕድሎችን ማግኘት ህልም ሆኗል፤ በንግዱም መስክ የሱን ታፔላ ሳይለጥፉ ለመንቀሳቀስ ማሰብ የዋህነት ነዉ፡፡ በጥቅሉ ኢህአዴግ በሀገር ዉስጥ ያለዉን የተቃዋሚዎች እንቅስቃሴና የህዝብ ተሳትፎ "የጋን ዉስጥ መብራት" ከማድረጉም በላይ ስልጣናቸዉን ከሚወዱና ለሱም ከሚሳሱቱ እጅ ስልጣን በሕዝብ ድምፅ ሊወጣ እንደማይችል እየወሰዳቸዉ ባሉ ተግባራት በግልፅ እያሳየ ነዉ፡፡
በስርዓቱ መሀንዲሶች ተለክተዉ የታጠሩ "ህጋዊ መንገዶች" ውስጥ በመንገታገት በሀገራችን ሕዝባዊ የሆነ አስተዳደር እናሰፍናለን በሚል የምናደርገዉ እንቅስቃሴ የአገዛዙን ዕድሜ ከማራዘም የሚያልፍ አይሆንም፡፡ ለዉጥን ለተራበዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዉጥን ያስገኝለታል በማለት የተጓዝንበትን መንገድና ያስገኘነዉን ዉጤት ገምግመን የሚያዋጣዉን መንገድ የምንመርጥበት ጊዜ አሁን ነዉ፡፡ በዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ፅኑ እምነት ብቸኛዉ አማራጭ በሁለንተናዊ መንገድ በኢህአዴግ ላይ ጫና መፍጠር ነዉ፡፡ የምንገባበት ሁለንተናዊ ትግል ቢቻል ኢህአዴግን ሰሚ ጆሮ እንዲኖረዉ ከማድረግ አልፎ በህግ የበላይነት አምኖና ለሱም ተገዢ ሆኖ የሀገሪቱን ተቋማት የህዝብ በማድረግ ነፃና ፍትሀዊ ምርጫ እንዲያካሂድ የሚያስገድድ፤ ይህ ካልሆነም ሕዝባችንን ከዚህ ስርዓት ለአንዴና ለሁሌም የሚገላግል ሊሆን ይገባዋል፡፡ በዚህ ረገድ የኢህአዴግን ባህሪ ጠንቅቀዉ በመገንዘብ የሀገራችንንና የሕዝቧን ሰቆቃ ለማቆም የጠራ ሀገራዊ ራዕይ ነድፈዉ ስርዓቱን ለመለወጥ ሁለንተናዊ የትግል እንቅስቃሴ ከጀመሩ፣ የተናጠል ጉዞን እርባናቢስነት ተረድተዉ ለተመሳሳይ ሀገራዊ ራዕይ ራሳቸዉን ካስገዙ ማናቸዉም ሀይሎች ጋር ተባብሮ ለመስራት በራቸዉን ክፍት ካደረጉ እንደ "ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ" ዓይነት ሀይሎች ጋር በጋራ መሰለፍ ወቅቱ የሚጠይቀን ሀገራዊ ግዴታ ነው፡፡
የሀገራችን ጉዳይ ይመለከተናል ለምንል ሁሉ ሀገራችንን ለማዳን የምንንቀሳቀስበት ጊዜ አሁን ነዉ - ቢዘገይም አላለፈም፡፡
የአላማና የዉጤት ሰዉ ይበለን!
|