| የግብርናው ነገር፤ እውነታው ሌላ፣ የሚባለው ሌላ |
|
|
| Monday, 11 May 2009 | |
|
የግብርናው ነገር፤ እውነታው ሌላ፣ የሚባለው ሌላ። Seid Hassan - Murray State University This e-mail address is being protected from spam bots, you need JavaScript enabled to view it May 8th, 2009 ክፍል አንድ፤ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ስናጤን ከማንኛውም ችግር የበለጠው የኑሮ ውድነቱና የዋጋ ግሽበቱ ሲሆን፤ሕዝቡን መፈናፈኛ አሳጥቶትና አስጨንቆትም መላው እንዲጠፋበት አድርጎታል። የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት በሄደባቸው ወቅቶች የሕብረተሰቡን ኑሮ ሁኔታ ጠጋ ብሎ ሲያይ (በተለይ በከተማው) አገሪቱን በጎበኘ ቁጥር ድህነቱ በአሰቃቂ ሁኔታ እየተስፋፋ መሄዱን ደጋግሞ ተገንዝቧል። እኔም ሆንኩ አሁን በቅርቡ የተወለዱባትን አገር ጎብኝተው የሚመለሱት ሰዎች በተደጋገመ መልክ ከሚናገሯቸው ቃላቶች መካከል "እኔ የማይገባኝና የሚገርመኝ ግን ኑሮ እንዲህ ተወዶ እያለ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዴት ሊቋቋመው እንደቻለ ነው?!" የሚል ነው። አንዳንድ በድህነት የተጎዱትን የሕብረተሰብ ክፍሎች ጠጋ ብለን ብናያቸውና ከአንደበቶቻቸው የሚወጡትን ስንሰማ "ዛሬ ምን በልቸ ልደር" በሚል ሀሳብ ለእለቱ የበሏትን ማግኘት እንጂ "የወደፊቱ ኑሯችንን እንዴት እናሻሽል" የሚለው ሃሳብ እንደ ቅንጦት ተቆጥሮ በአእምሮቸው እንደማይንሸራሸር ነው። በርካታ የቤተሰብ አባላትም፤ የጨለመውን ቀን ለማሳለፍ በተራ እንደሚመገቡም ሰምተናል፤ አይተናልም። አንዳንዶቹም "በቀን ሁለት ጊዜ መመገብ የሚባለው በቤታችን ውስጥ ከተከሰተ ወራቶች አልፈዋል" የሚሉም አሉ! እርሀብ ከመግደሉም አልፎ የለማኞችን ገመና አጋልጦ ያዋርዳል፤ ለበሽታ ይሰጣል፤ አካለ-ስንኩል ያደርጋል፤ ከርሃቡ የተረፉትን ልጆችም ይህችን ዓለም ለቀው እስኪሄዱ ድረስ አቅመ-ቢስና የአእምሮ ሲንኩል እንዲሆኑ ያደርጋል፤... አእምሮንም ያስታል። እኔ በገጠር ያድክሁ የገበሬ ልጅ ስለሆንኩ እነዚህን ክስተቶች በተግባር አይቻለሁ። እንደነዚህ ያሉት አባዜዎች እ.ኤ.አ. የ1974 ዓ.ም. እና በተደጋጋሚ የተከሰቱት ድርቆችና ርሀቦች ያደረሷቸውን ችገሮች በመከታተሌ፤ እነዚህን ችግሮች ሳስታውስ አሁንም እንባየ ዱብ፤ ዱብ፤ ይላል። በእርግጥ ብዙዎቻችን አንጋፋው ኢትዮጵያዊ ዘፋኝ ጥላሁን ገሰሠን ተከትለንም "ዋይ! ዋይ!..." ብለን እየዘፈን አልቅሰናል። ልዩነቱ ግን ከዚያ ሕብረተሰብ አብራኮች እንደመሆናችን መጠን ከማልቀስ ባሻገር ምን አድርገንለታል? ምንስ እያደረግን ነው? ሕዝባችንን ርሃብ እየፈደፈደው እያለ ለዋጋ ግሽበቱ ምክንያት ገብሬው ሀብታም ሆኖ የመሸመት ፍላጎቱ ስለጨመረ ነው ብለው ሲያላግጡበት ምን አድርግንለታል? የኑሮ ውድነቱን አስመልክቱ ትንሽ ለመጨመር ያህል፤ አሁን በቅርቡ የወጡት መረጃዎች እንዳመለከቱት የምግብ ዋጋወች ባለፉት የጥርና የየካቲት ወሮች (ያውም በመኸሩ ጊዜ!) ከ104% ባላነሰ አመታዊ አቆጣጠር ጨምሯል (በታህሣሥ ወር 96% ጨምሮ ነበር።) ለዚህም የጥሬ እህል ዋጋ መናር ዋናው መንስኤ የአቅርቦት ችግር ሆኖ እያለ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ግን አሁንም የችግሩ መንስኤ የኢትዮጳያ ሕዝብ ሀብታም ሆኖ የመግዛት ፍላጎቱ ስላደገ ነው ማለቱ ነው! ይባስ ብሎም አቶ መለስ ዘናዊ ባለፍው ዓመት (እ.ኤ.አ. 2008) መጨረሻ ላይ ሆን ተብሎ ተዘጋጅቶ ለፕሮፓጋንዳ በተሰራጨ ቪድዮ አማካይነት መንግሥታቸው ለሚከተለው የኤኮኖሚ እቅድ እና ፍልስፍና ምስጋና ይግባውና የኢትይጵያ ገበሬ ምርታማዊነቱ በየጊዜው እየጨመረ መጥቶ እድገቱ ኢትዮጵያ በአውሮፓ ታሪክ ታይቶ እንደነበረው "ህዳሴ" (Renaissance) ጋር እንድትወዳደር አድርጓታል። ህዳሴ ማለት "በአዲስ መልክ መወለድ" ("new birth'') ስለሆነም ኢትዮጵያ በአዲስነት እንደተወለደች ተድርጎ ስለሚቆጠር የኢትዮጵያ ሕዝብ ደስ ሊለው እንደሚገባ አቶ መለስ ሳይሰለቻቸው አተቱ። እድገቱ የሚማርክ ከመሆኑም የተነሳ የገጠሩ አሠራርና እድገት በከተማ ለሚኖረው ሕብረተሰብ አስተማሪ እንደሚሆንም አጥብቀው ገለጹ።[i] የከተማው ሕዝብም ከገጠሩ ሕብረተሰብ መማር እንዳለበት አስታወቁ። ይህም አልበቃ ብሎ አቶ መለስ እንዲህ አሉ፤ ኢትዮጵያ በአዲስ መልክ ከመወለዷ የተነሳ፤ በጣም ታዳጊ ከሆኑትና መለስተኛ ሀብታም ናቸው ከሚባሉት አገሮች ጋር በቅርቡ ትመደባለች! ይህ የፕሮፓጋንዳ ቃለ ምልልስ በቪዲዮ መልክ የተሰራጨው ወደ 10.4 ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያን በረሀብ እየተገረፉ ባሉበት ወቅት ነበር። አቶ መለስ ይህን ቃለ-ምልልስ ከሰጡ ከአንድ ሁለት ወራት በኋላ መንግሥታቸው እነዚህ ወገኖቻችን በርሀባ አደጋ ላይ ሊወድቁ የተቃረቡ መሆናቸውን እያወቁ እነደነበርና ሆን-ብሎ የፓርቲው ኮንግረስ እስኪገባደድ ድረስ የደበቀው መሆኑን የውጭ አገር እርዳታ ሰጭ ድርጅቶችኛ ሌሎችም ከመንግሥት ጋር ያልተያያዙ ድርጅቶች አመልክተዋል። በርግጥ የአቶ መለስ መንግሥት የኢትዮጵያን ኤኮኖሚ በሚመለከት ከእውነት የራቁ መግለጫዎችን እያጉተለተለ እንደሚያወጣ ሁሉም ተገንዝቦታል። ከዚያም አልፎ አንዳንድ ጊዜ ታዋቂ ኤኮኖሚስቶችንም (ለምሳሌ እንደነ Jeffrey Sachs, Joseph Stiglitz እና በቅርቡም Dani Rodrik)ን ወደ አዲስ አበባ እየጋበዙ በተዘዋዋሪ መልክ እራሣቸው በውሼት የቆለሉትን "የኤኮኖሚ እድገት" እንደ ገደል ማሚቶ እንዲያስተጋቡላቸው አድርገዋል። እንደነዚህ ያሉትን ታላላቅ የኤኮኖሚ ጠበብቶችን (ኢኮኖሚስቶችን)ም ሆነ የኤኮኖሚ "እርዳታ" የሚያደርጉትን ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ማታለልም ችለዋል። "ኤኮኖሚው ተወዳዳሪ በማይገኝለት መልክ እያደገ" ብለው እየነገሩን መሆኑማ፤ ኢትዮጵያ ከአለም ሕዝቦችና አገሮች ጋር ስትወዳደር በሙስና ከ163 አገሮች መካከል 138ኛውን ይዛ እያለችና ሙስናው ከመጠንባቱ የተነሳ ወደ ማፍያ አይነት አሠራር እየተለወጠ ባለበት ሁኔታ፤ 37% የሚሆነው ሕዝባችን በአሳቃቂ ድህነት ተወጥሮ እያለ፤ 81% የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በደንብ ተመግቦ የማያድር መሆኑና የቀን ገቢው ከሁለት የአሜሪካ ዶላር ያነሰ መሆኑ እየታወቀ፤ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠረው የኢትዮጵያ ሕዝብ በውጭ አገር የእህል እርዳታ እየተደገፈ እያለ፤ በበቂ መጸዳጃ ሊጠቀም የሚችለው የገጠር ሕዝብ (84% የሚሆነው ሕዝባችን) 7% ብቻ መሆኑ እየታወቀ፤ የአገሪቱ ደኖች ደምጥማጣቸው ጠፍቶ መሬታችን በነፋስና በዝናብ ጎርፍ በአስፈሪ መልክ ተጠርጎ እየሄደ መሆኑንና አገሪቱ ወደ በርሃነት በሚያስፈራ መልክ እየተለወጠች መሆኗን ብዙ አማላካቾች መኖራቸውን ተገዘበን እያለ፤ በተፈጠረው የአለምና የአካባቢው የአየር ጠባይ መለወጥ የተነሳ የውሃ እጥረት፤ተዳጋጋሚ ድርቆች እየተፈጠሩና የአካባቢ ሁኔታ መበከል የተነሳ እነዚህ ችግሮች አገሪቱን በጥፋት ላይ ያስቀመጧት መሆኑ እየታወቀ፤ አገሪቱን የመሬት ጥበት ወጥሯት እያለ፤ በተባበሩት መንግሥታት የሕብረተሰባዊ እድገት (Human Development Index) ኢትዮጵያ ከ177 አግሮች የ170ኛውን ቦታ ይዛ እያለች.... ነው። በነግራችን ላይ አንዳንድ ታዛቢዎች ከላይ የተጠቀሱትም ሆኑ ሌሎቹ ማወዳደሪያዎች ኢትዮጵያን ቸር በሆነ መልክ አስቀምጠዋታል ብለው ያምናሉ።
ይህ በዚህ ላይ እንዳለ፤ እስቲ ከዚህ በታች የሰፈሩትን ሁኔታዎች እንመልከትና በእውነትም የኢትዮጵያ ገበሬ ሀብታም ሆኖ ኢትዮጵያን ከ"ህዳሴ" ላይ ያደረሳት መሆኑን ወይም አለመሆኑን እንገንዘብ። ለጅማሯቻችን ያህል እስቲ ያገሪቱን አመታዊ ገቢ ሃብት በ3 ከፋፍለን እንመለከት (የ2008 ዓ.ም. ግምት)፤ ሀ) እርሻና ከእርሻ ጋር በተገናኘ ምርት የሚገኘው 45.9% - ለ) የኢንዱስትሪው ክፍል 12.9% ሐ) የፍጆታና መገልገያው (አገልግሎትን ሰጪ) ክፍል 41.2% በነዚህ ክፍሎች የተሰለፈው የሕብረተሰብ የሥራ ድርሻ ደግሞ፤ 1) በየእርሻና ተዛማጁ ክፍል የተሰማራው የሠራተኛ ክፍል = 80.2%፤ 2) በኢንዱስትሪው ክፍል የተሰማራው የሰው ሃይል = 6.6%፤ 3) በአገልግሎትና መገልገያ ክፍል የተሰማራው የሰው ሃይል = 13.2% (2005 ግምት)። ከዚህ በላይ ያሉትን መረጃዎችና አሃዞች አስቀድሜ ለማስቀምጥ የፈለግሁት፤ በአንድ በኩል አሁን የወጣው የሕዝብ ቆጠራ እንዳመለከተው፤ ወደ 83.8% የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በገጠር የሚኖር መሆኑን ለማስጨበጥና ቢያንስ 80% የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በግብርና ላይ የተሰማራ መሆኑን ለማሳየት፤ በአንፃሩ ደግሞ የእንዱስትሪውና የአገልግሎቱ ክፍሎች ተደምረው ወደ 19.8% የሚሆነውን የሰው ሃይል/አምራች ብቻ ያቀፉ መሆናቸውን ለማስገንዘብ ነው። በሌላው በኩል ደግሞ፤ አንባቢያን ሊረሱት የማይገባው ቁም ነገር የማንኛውም አገር ሀብትና ኤኮኖሚ ሊያድግ የሚችለው በሥራ ላይ በተሰለፈው የህብረተሰብ ችሎታና አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ጉልበቱንና እውቀቱን ተጠቅሞ በተግባር ላይ ማዋል የሚችል ከሆነ ብቻ ነው። በተጨማሪም የግብርናው ክፍል 60% ለሚሆነው የውጭ አገር ሽያጭ (exports) ምንጭ የሆነ፤ እስከ 90% የሚሆነውን የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ የኤኮኖሚ ክፍል ነው። ከዚህም በላይ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የኤኮኖሚ ግብርናውን አማካይ ያደረገው በግብርናው ላይ ነው። እንግዲህ የግብርናው ክፍል በአንድ በኩል የውጭ ምንዛሬን ለማስገኘት መጠቀሚያ ከመሆኑም በላይ፤ ለእንዱስትሪው ጥሬ እቃዎችን አቅራቢና አበርካች ይሆናል ማለት ነው። የግብርናው ክፍል ለእንዱስትሪው ባለማቋረጥ ጥሬ እቃዎችን በተሟላ ሁኔታ ሊያቀረብ ይችላል? ይህ የኤኮንሚ ክፍል (84% የሚሆነውን የሕዝብ ክፍል ያቀፈው) የኢትዮጵያን ኤኮኖሚ በየጊዜው እንድታድግ ሊያደርግ የሚያስችሉት ሁኔታዎች አሉን? እስቲ ችግሮቹን ከሞላ ጎደል በግርድፍ መልክ እንመልከታቸው። •1. የደኖች ተመንጥሮ መጥፋትና የመሬቱ መራቆት ፤ በሀገሪቱ ውስጥ የነበሩት ዛፎችና ደኖች ተመንጥረው ተመናምነዋል። የዛፎችና የደኖች መመንጠር በአገሪቱ ላይ በተዳጋሚ ለሚደርሱት ድርቆች ምክንያት ሆኗል። ኢትዮጵያ ደን-አላባ በመሆኗም የተነሳ በከፍተኛ የአየር/ነፋስና ጎርፍ መሬቷ እየተጠረገ መጥቷል። በዚህም የተነሳ ነው እንኳን ድርቅ ሊነካው ቀርቶ ደኑ ያስፈራራ የነበረው የአገሪቱ ክፍል በድርቅና በርሀብ መጠቃቱ አሁን ግልጽ ሆኖ የሚታየን። ከማንኝውም የበለጠ ማስረጃ የሚሆነን ግን፤ ወደ ገጠር ገባ ብለን፤ የቱን ይህል የኢትዮጵያ መሬት ወደ በረሃነት እየተለወጠ መምጣቱን ስንገነዘብ ነው። ይህን ችግር የዓለም ሕብረተሰብ ሁሉ ያወቀው ከመሆኑ የተነሳ፤ አንዳንድ ድሕረ-ገጾች እንኳ (ለምሳሌ እንደነ C.I.A. World Fact Book) እንዲህ ይላሉ፡ Ethiopia's poverty-stricken economy is based on agriculture, accounting for almost half of GDP, 60% of exports, and 80% of total employment. The agricultural sector suffers from frequent drought and poor cultivation practices. The country is faced with severe deforestation; overgrazing; soil erosion; desertification; water shortages in some areas from water-intensive farming and poor management. በእውነቱ እነዚህን ችግሮች ለመገንዝብ ብዙ መሄድ አያስፈልግም። ምሳሌዎች ለመጥቀስ ያህል፤ በወሎ ክፍለ-ሀገር ተወልዳችሁ ያደጋችሁ፤ ወደ ገጠር ወጣ ብላችሁ፤ የምንጮችን መድረቅ፤ የመሬቱን መቦርቦር፤ የዛፎችን መጥፋት በተጨባጭ ታያላችሁ። ብርዳም የነበረው ገራዶና ውሀውም ወደ ሞቃትነት ተለውጠው ወደ የስኳር አገዳ ማምረቻነት መለወጣቸውን ትገነዘባላችሁ። በደሴ ከተማ ያደጋችሁም፤ ደኑ ከመጥፋቱም አልፎ የቦርከና ውሀ መድረቁን (ከበፊቱ ሁኔታ ጋር ሲወዳደር)፤ የቦርከና ውሃ ይፈስበት የነበረው ቦታ በተጨናነቀ መልክ ወደ ከተማነት የተለወጠ ከመሆኑ አልፎ በአካባቢው የነበረው ጫካ ተመንጥሮ ያ የዝንጀሮ መስፈርያ የጅቦች መሸሸጊያ/መጮሂያ የነበረው ገደላዊ መሬት የሰው መስፈሪያ መሆኑን ትገነዘባላችሁ። በቦረና-ሳይንት የነበሩት የሽፍታ መሸሸጊያ የነበሩት ደኖች ድምጥማጣቸው ከመጥፋቱም በላይ፤ እረግረግ የነበሩ ቦታወች ደርቀው የሕዝብ መስፈሪያ ሆነውዋል። በደሴና በአዲአ አበባ ከታማዎች ዞር ዞር ብላችሁ ስታዩ ደግሞ ለማገዶ የሚሆን እንጨት ከመጥፋቱ የተነሳ በጣሊያን ጊዜ ተተክለው የነበሩ የባህር ዛፎች ድራሻቸው ጠፍቶ ሕብረተሰቡ ሥሮቻቸውን ከመሬት እየቆፈረ ሲጠቀምና መሬቱን ለጎርፍ ሲያጋልጥ ታያላችሁ። እኔ ባልተጓዝኩባቸው ክፍለ-ሀገሮች ተመሳሳይ ሁኔታዎች በሌሎች ክፍለ-ሀግሮች ተከስተተዋል ብየ አምናለሁ። አንዳንድ ኢትዮጵያን ጎብኝተው የሚመለሱ ተመሳሳይ ድርጊቶችን ያዩ መሆናቸውንም ገልፀውልኛል። •2. የአካባቢው የአየር ሁኔታ/ጠባይ መለወጥና ይህንንም አባዜ ለመቋቋም ዝግጁ ያለመሆን፤ በመካከለኛው ምስራቅ ነዳጅ ለማውጣት የሚደረገው ቁፋሮ የአካባቢውን - በተለይም በከፍተኛ አቀማመጥ የምትገኘዋን የኢትዮጵያን የአየር ጠባይ የቀየረው መሆኑን አንዳድንድ ሳንቲስቶች አመልከተዋል። ይህ የአየር ጠባይ መለወጥ ምናልባትም በኢትዮጵያ ላይ ፈጠን ባለ መልክ እየተመላለሰ ለመጣው ድርቅ አንዱ ምክንያት እንደሆነም የሚጠቁሙ ጥናቶች አሉ። በተጨማሪም የዓለም የአየር ሁኔታ መለወጥ (Global Warming) ኢትዮጵያን ለከባድና ተመላላሽ ድርቆች እንዲሁም በጎርፍ ለመጠረግ ዳርጓታል ይላሉ። •3. የሕዝብ ብዛትና የመሬት መንሸንሸን ችግሮች፤ በሀግሪቱ ውስጥ የሕዝብ ብዛት በየጊዜው መጨመርና መብዛት- የገጠሩ መሬት ሊሼከመው ከሚችለው በላይ የሕዝብ ቁጥር በአስፈሪ ሁኔታ እየጨመረ ነው። በዚህም የተነሳ የመሬት መንሸንሸን ግድ ሆኗል። መሬት ከመሸነንሸኑም የተነሳ መሬትን በዘማናዊ መልክ ማረስ አያስችልም። አለተቻለምም። ይህንንም በሚመለከት አንድ የኢትዮጵያ ኤኮኖሚስቶች ማህበር ቀደም ሲል ባቀረበው ጥናቱ እንዳመለከተው አንድ ገብሬ ከነቤተሰቡ የሚያርሰው አማካኝ ማሳ= 1.02 ሄክታር እንደሆነ፤ ወደ 37.6% የሚሆኑት ገብሬወች አማካይ የማሳ ድርሻ = 0.38 ሄክታር ብቻ መሆኑንና፤ ወደ 11% የሚሆኑት ገበሬወች ደግሞ ማሳ የሌላቸው ናቸው ሲል ዘግቧል። በዘመናዊ የእርሻ ቴኮኖሎጂ ተጠቅሞ የመገልገሉ ሁኔታ አሉታዊ ስለሆነ፤ የኢትዮጵያ ገበሬ የመረቃ ምርት አምርቶ በምርቱም ጠግቦ እንዲያድር ከተፈለገ፤ አዳዲስ የሚለሙ መሬቶች መኖር አለባቸው። በኢትዮጵያችን አዳዲስና ያልለሙ ምሬቶች ግን ብዙም የሉም። የሕብ ብዛት በብኩሉ የሚያስከተላቸው ሌሎች ተጨማሪ ጠንቆችም አሉ። ከነዚሁም መካከል፤ከተሞች በተዛባ መልክ እንዲስፋፉ ያደርጋል። በርካታው የሕብረተሰቡ ክፍል ወጣትና ምርተ-ቢስ እንዲሆን ያደርጋል። የተማረውና እውቀት ያለው የሕብረተሰብ ክፍል እንዲጫጫ ያደርጋል። እንግዲህ፤ የኢትዮጵያ ገብሬ በዘማናዊ የእርሻ መሳሪያ አመርቂ በሆነ መልክ ማምረት ካልቻለ፤ መሬትን መለጠጥ ስለማይቻል፤ ያለው አንዱ ዋና አማራጭ የሕዝብ ብዛትን መቀነስ ወይም ማገድ ነው። የሕዝብ ብዛቱን ከሚቀንሱት ጠቃሚ ፖሊሲዎች መካከል የመሬት ስሪትን መቀየር/ማስተካከል ነው። በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ግን የኢትዮጵያ የመሬት ሥሪት የሚቀየረው እኔ ሞቼ ከተቀበርኩ በኋላ ነው ሲል ፎክሯል። ይህ አነት ፉከራ ለፖለቲካ መጠቀሚያ ቢያገለግልም፤የመሬት ሥሪት የመለወጡን ጉዳይ ግን የተወሳሰብ እንዲሆን ያደርገዋል። ለመሆኑ የመሬት ጥበት ችግር አንዱና ዋናው መሆኑን የማያውቅ ማን አለ? •4. የለካፊ በሽታወች መብዣትና የጤና ጥበቃ አገልግሎት በበቂ አለመኖር - Low health service coverage and life expectancy aggravated by the prevalence of HIV/AIDS-፤ በግብርናው ላይ የተሰማራው ሕብረተሰብ በቂ የሆነ የጤና ጥበቃ የማይደረግለት ከመሆኑም በላይ ከመቸውም በላይ የልዩ ልዩ ለካፊ በሽታወች (ለምሳሌ የወባ የቲቢና የኤድስ የመሳሰሉት) ሰለባ እየሆነ መጥቷል። የወባ በሽታ ይታይባቸዋል መባሉ ቀርቶ ስማቸው በማይታወቅባቸው "ቀዝቃዛ ናቸው" በሚባሉት ስፍራዎች አካባቢዎች መታየቱ በጣም የሚሳፈራ ነው። በእቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት እንደ የወባና የኤዲስ በሽታዎች ላይ ጦርነት እንደመክፈት ፋንታ አላስፈለጊ የሆኑ ጦርነቶችን እየቀሰቀሰ ለትክክለኛው ጦርነት ሊውል የሚገባውን አገሪቱ ያሏታን ትንሽ አንጡራዎች አባክኗል/ያባክናል። ለምሳሌ ከኤርትራ ጋር የተደረገው ጦርነት ቢያንስ ሦስት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላርን የሚያህል ገንዝብ አስጨርሷል። •5. የመሬት ሥሪቱ ችግርና ገበሬው የመሬት ባለቤት ያለመሆን አባዜ- ገበሬው አሁንም ጭሰኛ መሆኑ፤ በተለይም ደግም በሥልጣን ላይ ያለው መግሥት- የደርግ መንግሥት የመሰረተውን የመሬት ሥሪት መሰረት በማደረግ-ያሰፈረው የመሬት ሥሪት/አያያዝ ባመጣው አባዜ የተነሳ፤ በአገረቱ ውስጥ ሊኖር የሚገባውን የምርት ውጤት/የሰብዕል ምርት (ፕሮዳክቲቪቲ) እየቀነሰው እንጂ እየጨመረው አለመምጣቱን ስንመለከት፤ በአንድ በኩል መግሥት ማረስ ለሚፈልግ ሁሉ መሬት እንደሚያድል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ቃል ስለገባ፤ ይህ "ቃል ኪዳን" በገበሬው አእምሮ ላይ የመሬት ችግር እንደሌለ ጫና ስላደረገበት ገብሬው ያለ-ጭንቀት (አባዜው ሳይገባው) እንዲወልድ/እንዲራባ/እንዲዋለድ ይገፋፋዋል። በሌላ በኩል ደግሞ መሬቱ የራሱ ስላልሆነ ገብሬው ለመሬቱ በጎርፍ መጠረግ ደንታ እንዳይኖረው ያደርገዋል/አድርጎታል። በዚህም የተነሳ ገበሬው መሬቱን በመንከባከብ እና የአካባቢ ብክልናን በመከላከል በኩል ግድየለሽ እንዲሆን ገፋፍቶታል። በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ አፈር በጎርፍ እየተጠረገ የሱዳንንና የግብጽን በረሀ ከማዳበሩም በላይ ወደ ሜድትራኒያን ባህር ተጠርጎ መግባቱን ሳያሰልስ ቀጥሏል። በ3ኛም በኩል ገበሬው ሊያርሰው የሚችለው የራሱ የሆነ መሬት፤ ማለትም "የኔ ነው፤ ማንም አይወስድብኝም፤ ልሸጠው፤ ልለውጠው፤ ለልጆቼ ላወርሰው፤ ወ.ዘ.ተ. እችላለሁ" ብሎ የሚንከባከበው መሬት፤ በግል-ንብረትነት ደረጃ የራሱ የሆነ በወልድ-አግድ አሲይዞ ሊበደርበትና ማምረቻ ነገሮችን የሚገዛበት- (raise capital) መሬት ሊኖረው ሲገባ፤ የጉዳዩንም አስፈላጊነት የኤኮኖሚ ጠበብቶች ቢመክሩም ቅሉ ይህ ባለመሆኑ የተነሰ ሀብቱና ሊጭምር የሚገባው ሰብል ባክኖ ቀርቷል። መሬት የገበሬው ባለመሆኑ የተነሳም ገበሬው ሊኖረው የሚገባው አቢይ ንብረት (capital) ባክኖ ቀርቷል። መሬት የግል ባለመሆኑ የተነሳ፤ አርሶ አደሩ ያሚስፈልገውን ያህል በራሱ አነሳሽነት (የራሱ መሆኑን ዋስትናው ስላልተረጋገጠና መረጋጋት ስለሌለ) በምርትና በእንክብካቤ (ለምሳሌ ዛፍ በመትከል፤ ውሀና አፈርን በመከባከብ) በሙሉ ልቡ እንዳይሳተፍ አድርገውታል። "ማረስ ለሚፈልግ ሁሉ መሬት ይሰጠዋል" የሚለው የመንግሥት ፖሊሲም፤ ምንም እንኳ ለሁሉም ገበሬ በበቂ ሁኔታ ሊዳረስ የሚችል መሬት ባይኖርም፤ ገብሬው "አንድ ቀን በቂ መሬት ይደርሰኛል" በሚል አስተሳሰብ፤ የሚወልዳቸው ልጆቹን ከግብርና ሌላ ተግባር ላይ እንዳይሳተፉ፤ ወይም ወደ ከተማ/ወደ የእንዱስትሪው የሥራ መስክ ፈልሰው እንዳይሄዱ ያግዳቸዋል። የኢህአደግ መንግስት የመሬት ፖሊሲን የፖለቲካው መሽከርከሪያ አድጎ ዘላቂ ልማትን በተቀላጠፈ መልኩ ለማስገኘት ሳንካ እንደፈጠረ ባለሙያዎች ያስቀምጣሉ። ለምሳሌ አቶ ሰለሞን ጎሹ በሪፖርተር ጋዜጣ በቅርቡ እንዳቀረቡት፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት አቶ ታፈሰ ኦሊቃ ‘Ethiopian Politics of Land-Tenure Policies under Three Rigimes፡ A carrot-and-stick Ruling Strategy' በተሰኘው [የጥናት] ፅሁፋቸው ግብርናው የኢኮኖሚውን እድገት በማፋጠን በምግብ ራስን ለመቻል፣ የሥራ እድል ለመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ እንዲሆን ለማድረግ፣ ለአዳጊ ኢንዱስትሪዎች ግብአትነት እንዲውል ለማድረግ መሬት ወሳኝ ቢሆንም መንግሥት ለፖለቲካ መጠቀሚያ ብቻ እያዋለው እንደሚገኝ ተችተዋል፡፡
በዚሁ ጋዜጣዊ ዘገባም፤ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ያሰፈረው የመሬት ስሪት፤ ገበሬውን ወደ ከተማ ፍልሰት እንዲያቆም አላደረገውም፤ በምግብ ራሱን እንዲችል አልረዳውምል። በሥለጣን ላይ ያለው መንግሥት፡ "ከኢሕአዴግ መቃብር ላይ ካልሆነ በቀር የመሬት መሸጥ መለወጥ የሚታሰብ አይደለም" ቢልም ነገር ግን መሬት የተለየና ስም ተሰጥቶት እየተሸጠና እየተለወጠ እንደሚገኝም አቶ ገብሩ አስራት ለአቶ ሰለሞን ጎሹ ገልጸውለታል፡፡ ጸሀፊው ቀጠለውም፡ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አባል አቶ አክሉ "የኢሕኢዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲና የሃብታም ገበሬዎች ጉዳይ ከምርታማነት፣ ከህዝብ ብዛት፣ አማራጭ ስትራቴጂ ካለመኖር፣ ከመስኖ ልማት ለመጠቀም ካለመፈለግ አንፃር ውጤታማ አለመሆኑንና ዛሬም ገበሬው በምግብ ራሱን እንዳልቻለ፣ ይልቁንም ተጠቃሚ የፓርቲው ካድሬ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ዶ/ር መረራ ኢሕአዴግ ገበሬውን በመሬት በማስፈራራት በግድ አባል እያደረገው መሆኑን አመልክተው መሬትን የሃገሪቱን ፖለቲካ ወደ ንግድ ለመቀየር ዋነኛ መሳሪያ እያደረገው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ገጠሩንና ግብርናን ማዕከል ያደረገው ስትራቴጂውም የሰው፤ የቁሳቁስና የቴክኖሎጂ ሀብትን ከከተማው ወደ ገጠር በማፍሰስ እየተገለፀ እንዳልሆነም ገልፀዋል፡፡ ገጠሩንና ከተማውን ለማመጣጠን እየተሰራ ያለውም ስራ ከዚህ ግባ የማይባል እንደሆነ ተናግረዋል። አቶ ገብሩ በከተሞች አካባቢ ያለ ዋስትና ገበሬዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈናቀሉ እንደሚገኙ ጠቁመው በመሬት አካባቢ የተሾሙ ባለስልጣናት በከፍተኛ ደረጃ እየበለፀጉ እንደሚገኙም አስረድተዋል። የገበሬው ተጠቃሚነት በህግ የተረጋገጠ ቢሆንም በተግባር የመሬት ደላላዎች እየተጠቀሙ እንደሚገኙ የገለፁት አቶ ገብሩ በሊዝ ለ50 ዓመት መሬት መከራየት ለመሬት ዋስትና ጥሩ ቢሆንም አስተማማኝ መንገድ መሆኑ አጠራጣሪ ነው ብለዋል።
•6. የመሬት ማዳበሪያው ያመጣው ችግር፤ ምንም እንኳ የመሬት ማዳበሪያው በአንዳንድ ቦታወች ምርት እንዲጨምር ቢያስችልም፤ በአንድ በኩል የኢሕአደግ ካድሬወች ገበሬውን የመሬት ማዳበሪያ ሳይወድ በግድ፤ ገብሬው ከሚችለው በላይ እንዲገዛ/እንዲከፍል በማድረጋቸው፤ ገብሬው በየጊዜው ወደ ድህነት ማጥ እንዲገብ ሆኗል። በዚህም የተነሳ ገበሬው በተበዳሪነት ተጠምዝዞ ስለተያዘ፤ እንዳውም እደኝነቱ አስጭንቆት ይገኛል። እነዚህም ተግባሮችና ሁኔታወች የገበሬውን ጉልበትም ሆነ የማምረት ፍላጎቱን እየቀነሱት መጥተዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ማዳበሪያ የለመደው መሬት የበለጠ ማዳበሪያ እንድነሰነሰለት ፈልጓል። አንዳንድ ጥናቶች እንዳመለከቱትም፤ በመሬቱ ላይ የተነሰነሰው ማዳበሪያ መጥፎና ለኢትዮጵያ መሬት የማይስማማ (ነገር ግን የኢሕአደግ ካድሬዎችን ካዝና ያደለበ - አቶ መለስም ያራ ተብሎ ከሚጠራው የኖርዌይ የማዳበሪያ አምራች ኩባንያ የ200,000 ዶላር ጉቦ ለመቀበል ወደ ኦስሎ (ኖርዋይ) በ2005 ዓ.ም. ሮጠው እንዲሄዱ ያደረገ) በመሆኑ፤ መሬቱን ከመበከሉም በላይ፤ በአንዳንድ ቦታዎች ምርቱን እንዲቀንስ አድርጎታል። •7. የገጠሩ ሕዝብ የፖለቲካው ሰልባ መሆንና መብቱ አለመከበሩ፤ የገጠሩ ሕብረተሰብ ለኢሕአደግ የፖለቲካ መሳሪያ ሰለባ ስለሆነና በየጊዜውም ለጭቆና ሰለባም ከመሆኑም በላይ፤ በየጊዜው ስብሰባ እየተጠራ የገበሬው ጉልበት እንድባክን ሆኗል። በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ኢ-ዲሞክራሲያዊ እስክሆነ ድረስ በመግሥቱና በሕብረተሰቡ መካከል ፉክቻው ስለሚቀጥልም የመንግሥቱ ካድሬወች ገበሬውን ማስቸገራቸውን ይጥሉበታል። የኢትዮጵያ ገብሬ በመንግሥት ካድሬወች ሌት ተቀን ጭካኔ በተሞላበት መልክ ስለሚያሸብሩትም እየተሰቀጠጠ ነው ኑሮውን የሚገፋው። የአእምሮ ነጻነቱን ያጣ የሕብረተሰብ ክፍል በመረቃ መልክ አምራች ሊሆን አይችልም። ምርት እንዲያድግ ከተፈለገ ገብሬውን ጠፍረው የያዙት የፖለቲካ ሥርዓቶች መወገድ አለባቸው ማለት ነው። •8. የኋላ ቀር የእርሻ አጠቃቀም ዘዴ፤ የኢትዮጵያ ገበሬ አሁንም የሚጠቀምበትን ኋላ ቀር የማምረቻ ዘዴ ምርትን እንዲጭምር አያግዝም። ምርቱ እንዲያድግ ከተፈለገ ገብሬው በዝናብ ከመተማመን ተላቆ በሰፊው ዘመናዊ ቴክኖሎግጂና በመስኖ ውሃ ተጠቅሞ ማምረት መቻል አለበት። በዘምናዊ የእርሻ መሣሪያ የሚታረሱ ሰፋፊ የመሬት እርሻወች መኖርም አለባቸው። በሳይንስና በቴክኖሎጂ ያለተደገፈ የግብርና ሥራ ሊያድግና ምርታዊም ሊሆን አይችለም። •9. የሰፋፊ እርሻወች ልማትና፤ የእርሻ ግባት አቅርቦቶች አለመኖር፤ የእርሻውን ምርት ለማሳደግ የሚያስችሉ የእርሻ ግባቶችና አቅርቦት አሁን ከሚደረገው በበለጠ ሊኖር ይገባል። የእርሻው ምርት ዕድገት በርካታ የሥራ መስኮች ሊፈጥር የሚችል እንዲሆንም መታቀድ አለበት። ይህ አሁን ገና በጅማሮ ላይ መሆኑ ቢታወቅም፤ አብዛኛውን ገብሬ ያሳትፍ እንድሆነ ገና አይታወቅም። የግብርናው ክፍል ለአገሪቱ የኤኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ሚና የሚጫወት እንዲሆን ከተፈለገ ሰፋፊ የእርሻ ልማቶች ተቋቁመው ባልተቋረጠ መልክ ለእንዱስትሪው ጥሬ እቃዎችን ማቀባል አለባቸው። በኤትዮጵያ ውስጥ ይህ ሁኔታ እስካሁን አልተከሰተም። እንዳዉም በቅርቡ የቡና ገባያን አስመልክቶ የታዩት ክስተቶች እንዳመለከቱት፤ መንግሥቱ ያቋቋመው የአቅርቦትና የንግድ ተቋም ችግሮቹ እንዲባባሱ አደርጓል። •10. በጥሩ መልክ አለመመገብና የምግብ እጥረት የተነሳ በርሀብ መጎዳት (ጠግቦ አለማደር)፡ ዛሬ እያንዳንዱን የገብሬ ሰውነት ስናይ፤ በሚደርስበት የምግብ እጥረት የተነሳ (በርከት ያለውን ሕዝባችንን እርሀብ እየቆላው ነው) ጤናውን ከማጣቱም በላይ፤ የማምረት ችሎታው እየቀነሰ እንጂ እየጨመረ አልመጣም። ሊመጣም አይችልም። የእርሻው ምርት እንዲያድግ ከተፈለገ ገበሬው በልቶ/ጠግቦ የሚያድርና ጤናማ መሆን አለበት። አሁን ወደ ገጠር ገባ ብለን የኢትዮጵያን ገብሬ የሰውነት ሁኔታ ስንመለከት በምግብ ማነስና የለካፊ በሽታዎች ሰለባ በመሆኑ የተነሳ ገብሬው የቀጨጨና ጉልበተ-አልባ መሆኑን እንገነዘባለን። •11. ሰላም መጥፋት/ማለቂያ በሌለው ጦርነት መጠመድ፤ በአገሪቱ ውስጥ ሰላም ስለሌለ፤ በየክፍለ ሀገሩ፤ በየመንደሩ፤ መለስተኛም ሆኑ ከፍተኛ ግጭቶችና ብጥብጦች፤ ሕዝቡን የኑሮና የአእምሮ ሰላም እንዲያጣ ስላደረጉት፤ "ነገ ምን ላምርት፤ እንዴት ምርቴን ላሻሻል...?" ብሎ ከማሰብ ሌላ "ነገሥ ምን መከራና ጭቅጭቅ ይመጣብኝ ይሆን፤ የዛሬውን የመከራ ቀን እንዴት ላሳልፍ፤ ጠምደው የያዙኝን የመንግሥት ካድሬዎች እንዴት ልቋቋማቸው እችላለሁ? ወ.ዘ.ተ.?" በመሳሰሉት እሉታዊ ችግሮች ተወጥሮ የሆነ መሆኑን ስንመለከት፤ ይህም ችግር አምራችነቱን የቀነሰበት መሆኑን እንገነዘባለን። •12. በ"ነጻ" እና በእርዳታ መልክ የሚታደለው የውጭ አገር እህል አባዜ፤ አገሪቱ ከመቸውም በበለጠ የእህል እጥረት እያጋጠማት ሰለመጣ፤ የውጭ አገር እህል በነጻ እንዲታደል የግድ ሆኗል። ይህ በነጻ የሚታደለውም እህል፤ ድርቅ ባልመጣባቸው አካባቢወች አምራች የሆኑትን ገብሬወች በጣም ጎድቷል (በነጻ የሚታደለው እህል ምርታቸውን ዋጋ-ቢስ ስላደረገው)። ገብሬውም ተግቶ እንዳይሰራ፤ እንዲዘናጋና፤ ለማኝ የመሆን ዝንባሌንም ማምጣቱ አልቀረም። •13. ለሀብታም አገር ገብሬዎች የሚደረገው ድጎማ ያመጣው አባዜ፤ ለአሜሪካ፤ ለአውሮፓና ለጃፓን አንድሁም ለደቡብ ኮሪያ ገብሬወች የሚደረገው ድጎማ በጣም ከፍተኛ ስለሆነ (ለምሳሌ ስዊዘርላንድ በምትባለው የአውሮፓ አገር ለአንድ እጅ የሰላጣ ችቦ ድጎማው እስከ 750% እንድሚሆን ከጥቂት ዓመታት በፊት ዎል ስትሪት ጆርናል በተባለው ጋዜጣ ተዘግቦ ነበር)፤ ድጎማ ማድረግ የማይችሉ አግሮችን- ኢትዮጵያን ጨምሮ- እየጎዳ መጥቷል። (በዓለም የንግድ ድርጅት አባላት መካከል ለተነሳውም ጭቅጭቅ አንዱና ዋናው ይህ ደጎማ ነው!) ምናልባት አንዳንድ አንባቢያን እንደ ኢትዮጵያ ያሉት አገሮችም ገበሬዎቻቸውን መደጎም አለባቸው ብለው ሊከራከሩ ይሞክሩ ይሆናል። ነገር ግን ይህ አስተሳሰብ ትክክል አይደለም፤ ተግባራዊም አይሆንም። በአንድ በኩል፤ ሊደረገ የሚታሰበው ድጎማ የበለፀጉ አገሮች ለገበሬዎቻቸው ከሚያደርጉት ድጎማ ጋር ሲወዳደር በጣም ትንሽ ስለሚሆን (የደሃ አገሮች ኪስ/ካዝና የተራቆጠ ስለሆነ)፤ ድጎማ ማድረጉ ዋጋ-ቢስ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በበለጸጉት አገሮች ውስጥ በግብርናው ሥራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው የሰው ሀይል በጣም ጥቂት ነው (ልምሳሌ በአሜሪካ አገር በግብርናው ላይ የተሰማራው የሰው ሀይል ከ2% አይበልጥም! በአንፃሩ ደግሞ ከ80% የማያንሰው የኢትዮጵያ የሰው/የሠራተኛ ሃይል በግብርናው ላይ የተሰማራ ስለሆነ፤ ማን ለማን ደጓሚ ይሆናል?) •14. ገበሬው በዘመናዊው የመብራት ሀይልና ንፁህ ውሃ መጠቀም አለመቻሉና ገበሬው ተበታትኖ ስለሚኖር በበቂ መልክ ልማትን ማካሄድን ለማድረግ ያለው ችግር (Highly dispersed villages/population.) ፤ በዘመናዊ የመብራት ሀይል የሚጠቀመው የገጠር ሕዝብ 2% ብቻ ነው። በገጠር የሚገኘው ሕብረተሰብ በየቦታው ተብታትኖ የሚኖር ስለሆነ እነዚህን ችግሮች መወጣት አልተቻለም፤ አይቻልምም። አንዱ መፍትሄ የመሬት ሥሪትን መለውጥና ገበሬው እነዚህን ችግሮች አውቆ ዘመናዊና እንደ የኤሌክትሪክና የውሃ መገልገያዎችን፤ ዘማንዊ የመፀዳጃ ቦታዎችን ለመጠቀም ያሚያስችሉ የመንደር/የከተማ አሰፋፈሮች ላይ ትብብር እንዲያደርግ ካልተደረገ ይህ ችግር ሊቀረፍ አይችልም።
ተበታትኖ መኖር የልማት ሥራዎችን ፋይዳ-ቢስ ያደርጋቸዋል። አንዳንድ ጥናቶች እንዳመለከቱትም የሳሳው የሠፈራ (የመንደር አመሠራረት) ከሰሃራው በርሃ በታች ለሚገኙት አገሮች የልማት ሥራን ለማቋቋም ብዙ እንደሚያስወጣቸው (ወድ እንደሚሆንባቸው) ነው። ይህም ችግር ተሰባስቦ በመኖር/በመሥራት ሊገኝ የሚቻለውን ጥቅም (benefit from economies of agglomeration) ተጠቃሚ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል። አንዳንድ ጥናቶች እንዳመለከቱት ከሰሀራ በርሃ በታች ለሚገኙት አገሮች አንድ የልማት ሥራን ለማቋቋምና ተግባራዊ ለማድረግ በነፍሶከፍ እስከ 400 የአሜሪካ ዶላር የሚፍጅባቸው ሲሆን፤ በአንጻሩ ደግሞ በሌሎች አገሮች የነፍሶከፍ ወጪ የዚህን ግማሽ ብቻ ነው። በእውነቱ በአንዲት አገር ውስጥ የልማት ውጥኖች/እቅዶች ተግባሮች ሲደረጉ በርከት ያሉ ነገሮች መመዘን አለባቸው። ከነዚህም መካከል፡ 1) የልማት ሥራ በአካባቢ ብከላ ያለው አሉታዊ ተጽእኖ፤ 2) ጥቅሙና ጉዳቱ፤ በተለይም፤ 3) የተዘራጋው የለማት ሥራ ለተጠቃሚው በአቅርቦት ሲቀርብ ተጠቃሚው ግልጋሎቱን ለመጠቀም ፍላጎት ያለው መሆኑንና ሊክፍል የሚችል መሆኑንን፤ 4) የተዘረጋውን ልማት ለመንከባከበ በየአመቱ የሚያስወጣው ወጪ (operating and maintenance cost) ...ወ.ዘ.ተ. ሊሸፍን መቻሉን ነው። በነገራችን ላይ በኢትዮጵያና በአንዳንድ አፍሪካ አገሮች እየተዘረጉ ያሉት የልማት ተቋሞች ከ1 እስከ 4 የተዘረዘሩትን ችግሮች ያልቀረፉ/የማይቀርፉ ስለሆኑ፤ ልማቶቹ እንደ ኪሳራ መቆጠር አለባቸው ብለው የሚያቀርቡ ብዙ አዋቂዎች አሉ። የገጠሩ ሕዝብ በከተማ መልክ እንዲኖር ማድረግ በርካታ ጥቅሞችን ያመጣል፤ ችግሮችንም እንዲቀረፉ ይረዳል። በአንድ በኩል የመሬት ጥብት የበለጠ እንዳያስቸግር ያግዛል። በሌላ በኩል ደግሞ፤ በከተማ ተከማችቶ የሚኖረው ሕዝብም ትምህርት ቤቶችን፤ የመብራት ሀይል ማመንጫዎችን፤ የውሃ ጉድጓዶችን፤ የመፀዳጃ ቦታወችን ተባብሮ እንዲሠራና በቀላሉና በቀነስ ወጪ እንዲጠቅም ያስችሉታል። እስካሁን የተገኙት ተመክሮዎችና ጥናቶች እንዳመለከቱትም፤ በከተማ መልክ ሕዝባቸውን እንዲሰባሰቡ ያደረጉ ሀገሮች የኤኮኖሚ እድገትንና የኑሮ መሻሻልን አድርገዋል። •15. ለውጭ አገር ግለሰቦችና መሪዎች በመታደል ላይ ያለው ለም መሬታችን ወደፊት የሚያስከትለው ችግር፤ በአንድ በኩል መሬቱ ከጭሰኞች የሚነጠቅ ከሆነ ገብሬወች እንዲፈናቀሉ ያድርጋል። ይህም ጉዳይ ግጭትን ሊያስከትል ይችላል። በሌላ በኩል መሬቱ በጭሰኞች ያልተያዘና ያልታረሰ ከሆነ፤ ለምለም መሬታችን በሀገር ከበርቴወች ሥር እንዳይሆን ከማድረጉም በላይ በሌሎች አገሮች እንደተከሰተው ሁሉ የውጭ አገር ከበርቴዎች ለአገራችን የእካባቢ መበላሸት/ መበከል ምክንያት ሊሆኑም ይችላሉ። ይህ ከሆነም በአንድ በኩል በውጭ አገር ከበርቴዎችና በሀገራችን ከበርቴዎች መካከል፤ በሌላ በኩል ደግሞ በውጭ አገር ከበርቴዎችና በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ መካከል አለመስማማትንና ግጭትንም ሊፈጥር ይችላል። አገሪቱ ወደ ድህነት ባሽቆለቆለች ቁጥር ግጭቱ ሊስፋፋ እንደሚችልም መጠበቅ አለበት። •16. የአገሪቱ ሕብረተሰብ በክልል/ጎሳ በመከፋፈሉ የተነሳ ሰፊ የሆነ ገባያና የሕዝብ ብዛት ያለው ተጠቃሚ የሚያስፈልጋቸው የልማት ተግባራት በሥራ ላይ ሊውሉ አለመቻላቸው። The separation of regions via competing ethnicities makes it impossible to build a well-functioning business and infrastructure, such as internet servers, mobile phones, water wells, electricity power lines, fright, and airports, etc. ለማጠቃለል ያህል፤ ማንም እንደሚያውቀው ለአንዲት ኤኮኖሚ እድገት ወሳኙ ጤነኛ የሆነ፤ ጉልበት ያለው፤ አእምሮው ነጻ የሆነ፤ የተማረ፤ ዘመናዊ መሣሪያን ተጠቃሚ የሆነ የሰው ሀይል እነደመሆኑ መጠን፤ በተጨማሪም የማምረት ችሎታውንና ፍልጎቱንም ሊያሳድጉ የሚችሉ ፖሊሲዎች አስፈላጊ ናቸው። ነገር ግን ይህ ወደ 84% የሚሆነው ሕዝባችን በሚሰቀጥጥ መልክ በአግባቡ ካለመመገብ፤ የአስከአፊ በሽታዎች ሰለባ በመሆን፤ በምግብ እጥረትና በርሀብ እየተገረፈና እየረገፈ ባለበት ሁኔታ እድገት ይመጣል ብሎ ማሰብ ቅዤት ነው። የሕዝብ ብዛት (ያውም አምራችነት የሚያንሰው ወጣትና ልጅ የሆነ ሕዝብ) የሚያስከትለውን (ያስከተለውን) አባዜም አንርሳ። እድገት አለ ብሎ መናገር ደግሞ በብዙ ሚሊዮን ሕዝብ ህይወት ላይ መቀለድ ነው። "ኤኮኖሚው ተወድዳዳሪ በማይገኝለት መልክ እያደገ ነው፤ ገብሬው ሃብታም በሞሆኑ የመግዛት ፍላጎቱ ጨምሯል..." ተብሎ ውሼት ቢቆለል የሚያመጣው ፍይዳ የለም! በአንዲት ሃገር ውስጥ የሚኖረው የሰው ሀይል ጉልበቱንና እውቀጡን በንቃትና በነፃነት በመጠቀም ብቻ እንጂ የአንዲት የአገር ሀብትና ኤኮኖሚ ሊያድግ የሚችለው ስለተዋሸለት አይደለም። በነገራችን ላይ በቅርቡ የወጣው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አመታዊ መግለጫ እንዲህ አለ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በየዓመቱ ወደ 3% ስለሚያድግ፤ መንግሥት ከሚገልፀው የኤኮኖሚ አመታዊ ጭማሮ ላይ እድገቱን እወነታዊ ለማድረግ ይህንኑ 3% ቀንሱበት ይላል! ጥሩ ጅማሮ ነው፤ ነገር ግን ግሽበቱ በኤኮኖሚው እድገት ላይ ያለውን አሉታዊ ሁኔታ መቸ ይሆን ይቀነስ (ይስተካከል) የሚሉን?
በእውነቱ ከላይ ባጭሩ የተዘረዘሩት ችግሮች አንዳዶቹ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የፈጠራቸውም አይደሉም። እንዳውም አንዱ መንግሥት ሄዶ ሌላው ሲተካ የሚኖሩ ዘላቂ ችግሮች ናቸው። አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ከሌሎቹ የሚለየው እነዚህን ችግሮች ለማቃለል ችሎታው ያነሰ (የሌለው) መሆኑና በተግባር ሲታይ ችግሮቹን ለመቅረፍ ፍላጎትም የሌለው መሆኑ ነው። ችግሮቹ 84% የሚሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ወጥረውት እያሉ ችግሮቹን የሚሸፋፍን መሆኑም በተደጋጋሚ ታይቷል። ከላይ የተዘረዘሩት ጉዳዮች የሚያስከትሏቸው አሉታዊ ችግሮች በጋራ፤ በድምርና በሂደት አብረው እንጂ በተናጠል መታየት የለባቸውም። በእውነቱ ችግሮቹን በድምርና በሂደት መለክ ስንመለከታቸው፤ አንዳንድ ጥያቄዎች በአእምሮችን ላይ መንሳፈፋቸው አይቀርም። ለምሳሌ "ይህችን አገር ድሮ ወደ ነበረችበት ሁኔታ ለመመለስ ቀርቶ (ድሮ የነበርችበት ሁኔታ የሚናፍቅና የሚማርክ ከሆነ)፤ አሁን ባለችበት አስቸጋሪ ሁኔታ እንኳ ትቆያለችን?" የሚለው ጥያቄ ይመጣብናል/ሊመጣብን ይገባል። አስበን ስናሰላስልም መፍትሄው ይጠፋብናል፤ እንዳዉም ጨልሞብን በጣም ይጨንቀናል። የኢትዮጵያም ሕዝቦች ስለጨነቃቸውውም ነው የተውለዱባትን፤ እትብታቸው የተቀበርችባትን፤ ወገኖቻቸውን/ቤተሰቦቻቸውን/ፍቅረኞቻቸውን...፤ ውድ አገራችውን እየለቀቁ እየተሰደዱ ያሉት። ከዚህ የበለጠ መረጃ ምን ይኖራል? በእውነቱ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች እንደዚሁ ከቀጠሉ ኢትዮጵያ በኤኮኖሚ መናወጥ የተነሳ እንዲትበታተንም ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ! መረሳት የሌለበት ነገር ደግሞ፤ በአኳያው በሌላው ዓለም የሚገኙ ሕብረተሰቦችና አገሮች በሰው ልጅ እውቀት የተደገፈ እኮኖሚን (knowledge economy) ተጠቅመው እየገሰገሱ ስለሆነ አገራችን አሁን ባለችበት ሁኔታ ብትቆይ እንኳ ወይም የኤኮኖሚ እድገቷ ከተወዳዳሪዎቿና ከዓለም ሕብረተሰብ ጋር የማይመጣጠን ከሆነ፤ ተፎካካሪዎቿ ጥለዋት ሲያልፉ፤ ኢትዮጵያና ህብረተሰቦቿ ወደኋላ ይቀራሉ። አገሪቱም የተማሩና የማምረት አቅም ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎቿንም ለቀደሟት አገሮች አስረካቢ እንደሆነች ትቀራለች። አእምሮዋ እየደማ ይቆያል። እንዳዉም የአገሪቱ የፖለቲካና የኤኮኖሚ ሁኔታወች (ፖሊሲዎች) አሁን ባሉበት አካሄድ ከቀጠሉ፤ የበለጠ ሕዝባዊ ሰቆቃ (human suffering)፤ የበለጠ የኤኮኖሚና የሕብረተሰብ እንድሁም የፖለቲካ ችግሮች ቀስ በቀስ ሊከስቱ ይችላሉ። ያለመረጋጋትና የመፈናቀል/የመፍለስ ችግሮቻችን እየበዙ መጥተውም ለጎረቤት አገሮችና ለመላው ዓለምም የሚደርሱ እንደሚሆኑ ሊታየንም ይገባል። እኔ እንደሚታየኝ ከሆነ የመሬት ስሪቱና በግብርናው ላይ የተሰማራው ሕብረተሳብችን ችግሮች በቀላሉ የሚቀረፉ አይደሉም። አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥትም "ገብሬው ጠግቧል፤ ነጻ ስለሆነ ለምርቱ የፈልገውን ዋጋ መጠየቅ ችሏል. ወ. ዘ. ተ." ብሎ ከመዋሸቱም በላይ የመሬት ሥሪቱን ለመለወጥ እንዳይመችና የተወሳሰቡ እያደርጋቸው ስለሆነ ብዙ ልንጠብቅም አይገባንም ይሆናል። ነገር ግን ለኢትዮጵያና ለሕዝባችን የተሻሉ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ የምንፈልግ ሁሉ ችግሮቹን ለመቅረፍ እንዲንችል ካሁኑ በጥናት መልክ (አዋቂዎችን ባሳለፈ መልክ) ለማየት መጀመር አለብን። ማስታወሻ፡የዚህ ጽሁፍ ተከታዮች የእንዱስትሪውንና የአገልግሎቱን የኤኮኖሚ ችግሮች ከተነተኑ በኋላ፤ በመጨረሻም፤ የኢትዮጵያን ኤኮኖሚ ወጥረው የያዙት ችግሮች ይቀርባሉ። እስከዚያው ቸር ይግጠመን።
ዋቢዎች፤ •1. ይህ ፀሀፊ በተልያዩ ጊዜ ያወጧቸው ጽሁፎች •2. የተለያዩ የሪፖርተር ጋዜጣ እትሞች •3. የዚህ ጽሁፍ ተከታይ በሆኑት መጣጥፎች የሰፈሩት መረጃዎች •4. http://siteresources.worldbank.org/INTAFRICA/Resources/AICD_exec_summ_9-30-08a.pdf
[i] በኔ አተረጓጎም ግን "ፓርቲያችን የገጠሩን ሕብረተሰብ በደንብ ለጉሞ ስለያዘው፤ የከተማውንም ሕብረተሰብ እንደዚሁ ማድረግ አለብን" ነው! Comments (0)
![]() Write comment
|